ቀጥታ፡

በአሁን ጊዜ በኢትዮጵያ የዚካ ቫይረስ ስጋት የለም - የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

ህዳር 18/2012 በአሁን ጊዜ በኢትዮጵያ የዚካ ቫይረስ ስጋት አለመኖሩን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። የእንግሊዝ መንግስት ባለፈው ሰኞ በኢትዮጵያ የዚካ ቫይረስ ስጋት በመኖሩ በተለይ ነፍሰጡር እናቶች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማስጠንቀቁ ይታወሳል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የዚካ ቫይረስ ስጋት አለመኖሩን አስታውቋል። በኢንስቲትዩቱ የበሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ወሰን ለኢዜአ አንዳስታወቁት የዚካ ቫይረስ አምጪ ትንሽ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የዓለም አገራት ትገኛለች። ይሁንና "ትንኟ አለች ማለት በሽታው ተከስቷል" ማለት አለመሆኑን ገልጸው፤ በአሁኑ ጊዜ በየትኛውም የአገሪቷ አካባቢ  በትንኟ አማካኝነት በቫይረሱ የተያዘ ሰው የለም ብለዋል። የእንግሊዝ መንግስት ለዜጎቹ ያሰራጨው መረጃ ከምን ተነስቶ እንደሆነም ግልጽ አለመሆኑን ተናግረዋል። የዚካ ቫይረስ 'ኤደስ' በምትባል የወባ  ዝርያ የሆነች ትንኝ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው በደም ልገሳ፣ ከእናት ወደ ልጅ እንዲሁም በግብረ ስጋ ግንኙነት ጊዜ የመተላለፍ ዕድል አለው። እንደ አቶ መስፍን ገለጻ ኢንስቲትዩቱ በሁሉም ክልሎች በየቀኑ የበሽታዎችን ቅኝት እያደረገ ሲሆን በተለይም በአሁኑ ጊዜ 'ኤደስ' የምትባለው የትንኝ ዝርያ በሞቃታማ አካባቢዎች መኖሯ ተረጋግጧል። ትንኟ የዚካ ቫይረስን ጨምሮ ቹጉንኩኒያ፣ ወባና ሌሎች የበሽታ አይነቶችን ማስተላለፍ ትችላለች። በድሬዳዋ የተከሰተው የቺንጉንጉኒያ በሽታ በዚች ትንኝ አማካኝነት መሆኑን አስታውሰው፤ እስካሁን ግን በትንኟ አማካኝነት በዚካ ቫይረስ የተጠቃ ሰው አለመኖሩንና ስጋቱም እንደሌለ ተናግረዋል። በተለይም አፋር፣ ሶማሌና ድሬዳዋን የመሳሰሉት ሞቃታማ የአገሪቷ ክፍሎች ላይ ትንኟ የምትገኝ ሲሆን፤ ለትንኟ መራቢያ የሚሆኑ ቦታዎችን በማጽዳትና በየጊዜው ቅኝት በማድረግ የመከላከል ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል። በአለም ጤና ድርጅት ሪፖርት መሠረት በብራዚል የመጀመሪያው የበሽታው ስርጭት የታየ ሲሆን ዚካ ቫይረስ በ21 ሀገሮችና በአሜሪካ ግዛቶች ተሰራጭቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም