ኢህአዴግ የሚያካሂደው ውህደት በፌዴራል ስርዓቱ ህልውና ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የለም... ፖለቲከኞች - ኢዜአ አማርኛ
ኢህአዴግ የሚያካሂደው ውህደት በፌዴራል ስርዓቱ ህልውና ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የለም... ፖለቲከኞች
ህዳር 18/2012 የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ የሚያካሄደው ውህደት በአገሪቱ የፌዴራል ስርዓት ህልውና ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንደሌለ ኢዜአ ያነጋገራቸው ፖለቲከኞች ገለጹ። ገዢው ኢህአዴግን በጥምረት የፈጠሩት አራቱ ፓርቲዎችና ሌሎች አጋር የፖለቲካ ድርጅቶች በመወሃድ "የብልፅግና ፓርቲ" በሚል ስያሜ አንድ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ለመመስረት በሂደት ላይ መሆናቸው ይታወቃል። አንዳንድ ወገኖች ግን በብሄር ስም ተቋቁመው የሚንቀሳቀሱትን እነዚህን ፓርቲዎች በማዋሃድ ወደ አንድ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ማሸጋገር አገሪቱ የምትከተለውን የፌዴራል ስርዓት አደጋ ላይ ይጥለዋል የሚል ስጋት ሲያቀርቡ ይደመጣል። ሆኖም ኢዜአ ያነጋገራቸው አንጋፋ ፖለቲከኞች የፌዴራል ስርዓቱ በአገሪቱ ህገ-መንግስት መሰረት የተዋቀረ በመሆኑ ከውህደቱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም፤ በፌዴራላዊ ስርዓቱ ህልውና ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅእኖም አይኖርም ይላሉ። የፖለቲካ ምሁሩ ዶክተር ዲማ ነጎ እንደሚሉት፤ የአገሪቱ ህገ መንግስት በህዝብ ይሁንታ እስካልተቀየረ ድረስ አሁን ያለው የፌዴራል ስርዓት አወቃቀር ሊቀየር አይችልም። ባለፉት 28 ዓመታት በኢትዮጵያ የነበረው የፌዴራል ስርዓት በትክክል ተግባር ላይ አልዋለም ሲሉም ያመለክታሉ። ውህደቱ ግን በአገሪቱ ትክክለኛውን የፌዴራሊዝም ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ነው ዶክተር ዲማ የሚናገሩት። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ሊቀ መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ተግባራዊ በተደረገው የዘውግ ፖለቲካ በህዝቦች መካከል ከአንድነት ይልቅ ልዩነት እንዲፈጠር ማድረጉን አንስተዋል። በአሁኑ ወቅት የኢህአዴግ ውህድ ፓርቲ መሆን በፌዴራል ስርዓቱና በመንግስት መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ለማሳየት እንደሚያስችልም አስረድተዋል። እንደ አቶ የሺዋስ ገለጻ ውህደቱ የፌዴራል ስርዓቱ ከመንግስት ጋር የሚኖረውን ቁርኝት በግልጽ ለማሳየት ዓይነተኛው መንገድ ይሆናል። ውህደቱ ከዚህ በፊት በመንግስት ስልጣን ላይ የሚታየውን ከችሎታ ይልቅ በፓርቲ ኮታ የመመደብ ችግርን የሚያስቀር እንደሆነም ዶክተር ዲማ ጨምረው አመልክተዋል። ኢህአዴግ ከግንባርነት ወደ ውህድ ፓርቲ የሚያደርገው ሽግግር የፌዴራል ስርዓቱን ወደ አህዳዊ ስርዓት ሊቀይረው ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው ወገኖች በፓርቲ ፕሮግራምና በህገ መንግስት መካከል ያለውን ልዩነት ካለመረዳት የሚመነጭ ስጋት ያደረባቸው እንደሆኑም አቶ የሺዋስ አስረድተዋል። ዶክተር ዲማ በበኩላቸው ''የመንግስት አወቃቀር እና የፓርቲ አደረጃጀት የተለያየ በመሆኑ ኢህአዴግ ከግንባርነት ወደውህድ ፓርቲ መሸጋገሩ የፌዴራል ስርዓቱን ወደአህዳዊ ስርዓት አይለውጠውም'' ብለዋል። አቶ የሺዋስ እንዳሉት ባለፉት ጊዜያት በግንባሩ የተላለፉ ውሳኔዎች በሙሉ አጋር ፓርቲዎችን ያገለለ በመሆኑ የውህደት ጥያቄው ለበርካታ ጊዜያት ሲነሳ የቆየው ከአምስቱ አጋር ፓርቲዎች ነበር። የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ግንባርን /ኢህአዴግን/ ወደ ብልጽግና ፓርቲ የማሸጋገሩ ጉዳይ በግንባሩ ስራ አስፈጻሚ እና ምክር ቤት በቅርቡ ውሳኔ አግኝቷል። ትናንት ህዳር 17 ቀን 2012 ዓ.ም የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኦዴፓ/ እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/ ባካሄዷቸው ጠቅላላ ጉባኤም ወደ ብልጽግና ፓርቲ ለመዋሃድ ውሳኔ አሳልፈዋል። በተመሳሳይ ከቀናት በፊት ደግሞ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አብዴፓ/ እና የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ሶዴፓ/ ወደ ብልጽግና ፓርቲ በጠቅላላ ጉባዔ ለመዋሃድ ውሳኔ ማሳለፋቸው ይታወሳል።