ቀጥታ፡

የጎንደር ፋሲለደስ ትምህርት ቤትን ከመፍረስ አደጋ ለመታደግ ገንዘብ ማሰባሰብ ተጀመረ

ጎንደር ኢዜአ ህዳር 18 ቀን 2012 ዓም -በጎንደር ከተማ ጥንታዊው የፋሲለደስ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ከተጋረጠበት የመፍረስ አደጋ ለመታደ የገንዘብ መሰባሰብ ስራ መጀመሩ ተገለጸ። የትምህርት ቤቱ ህንጻ በደረሰበት የመሰንጠቅ አደጋ 13 የመማሪያ ክፍሎቹ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸው ተነግሯል። የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ እንዳለ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት ትምሀርት ቤቱን ከተጋረጠበት የመፍረስ አደጋ ለመታደግ በውጭና በሀገር ውስጥ የሚገኙ የቀድሞ ተማሪዎች፣ ነዋሪዎችና ተቋማትን በማስተባበር ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ ተጀምሯል ። የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪዎችንና የአካባቢው ተወላጆችን ያሳተፈ 29 አባላት ያለው ኮሚቴ ተዋቅሮ ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ። ትምህርት ቤቱን ጥንታዊና ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ ለማደስና ለማስፋፋት የ68 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት መቀረጹን ገልፀዋል ። ለትምህርት ቤቱ በሚደረግለት ማስፋፋፊያ 39 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ባለ ሶስት ፎቅ ህንጻ፣ ቤተ- መጻህፍትና የአስተዳደር ቢሮች እንደሚገነቡ አመላክተዋል ። በተጀመረው የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ በአሜሪካ ከሚገኙ የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪዎችና የአካባቢው ተወላጆች ከ75 ሺህ ዶላር በላይ መገኘቱን ጠቅሰዋል። በጎንደር ከተማ ከሚገኙ የተማሪ ወላጀችም ከ750 ሽህ ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል ። የጎንደር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አማረ መስፍን ትምህርት ቤቱ ባጋጠመው እርጅና በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን ጠቁመዋል ። ያለበት የክፍል ጥበት በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን አመልክተዋል። ትምህርት ቤቱን ጥንታዊ ይዘቱን ሳይለቅ ለማደስና ለማስፋፋት ከቀድሞ ተማሪዎችና ከነዋሪዎች እየተደረገ ካለው ድጋፍ በተጨማሪ ከአማራ አቀፍ ልማት ማህበር ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ። እንደ ኃላፊው ገለጻ የትምህርት ቤቱ እድሳትና ማስፋፊያ ግንባታ ስራ የፊታችን ጥር ወር ተጀምሮ በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ። ትምህርት ቤቱ በዚህ አመት 3ሺህ 250 ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ መሆኑ ታውቋል ። የጎንደር ፋሲለደስ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት 78 ዓመት እድሜ ያለው ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም