ቀጥታ፡

ውህደቱ ክልሎች በአገራቸው ጉዳይ ላይ ከታዛዥነት ወደተሳታፊነት እንዲሸጋገሩ ያስችላቸዋል - ወጣቶች

ኢዜአ፤ ህዳር 18/2012 የኢህአዴግና አጋር ድርጅት ፓርቲዎች መወሃድ የክልል መንግስታት በአገሪቱ አጠቃላይ ጉዳይ ላይ ከታዛዥነት ወደተሳታፊነት እንዲሸጋገሩ ያስችላቸዋል የሚል ተስፋ እንደፈጠረላቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የወጣት ማህበራት ገለጹ።

ገዢው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) እና አጋር በሚል የሚታወቁት የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማወሃድ አንድ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ለመመስረት እንቀስቃሴ እየተደረገ ነው።

አጋር ተብለው የሚጠሩት የክልል ፓርቲዎች በሀገሪቱ የተለያዩ የሃላፊነትና ውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ተገልለው ቆይተዋልም ሲሉ ነው ሂደቱን በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የወጣት ማህበራት መሪዎች የሚናገሩት።

የፓርቲዎቹ ውህደት በሀገሪቱ ተግባራዊ የተደረገውን የፌዴራሊዝም ስርአት በትክክለኛው መንገድ በማስኬድ ፍትሃዊ ተሳትፎንና ተጠቃሚነትን ለማምጣት እንደሚያግዝ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል።

አንድ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ መመስረቱ በተለይ የመላው አገሪቱን ወጣት ማህበረሰብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር ያግዛል ሲሉም ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በተለይ አጋር ተብለው በሚጠሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመሩ ክልሎች በአገሪቱ ወሳኝ ጉዳዮች ቀጥታ ተሳታፊነታቸው አነስተኛ ነበር ሲል የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወጣት አብዱ ኢብራሔም ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወጣት ሞሐዲን ናስር በበኩሉ ፌዴሬሽኑ የወጣቶች ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ኃብታዊና ማሕበራዊ ተሳትፎን ለማሳደግ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ይሰራል ብሏል።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በግንባር ደረጃ የተዋቀሩና አጋር በሚባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ውህደት ለመፍጠር በጋራ የጀመሩት እንቅስቃሴ ወጣቱን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተስፋ አለኝ ሲልም አክሏል።

ውህዱ ፓርቲ ውጤታማ ይሆን ዘንድ የብዙሃኑን ወጣት ትክክለኛ ጥያቄ ለመመለስና ተሳትፎውን ለማሳደግ ብቃት ያለው አመራር ሊኖረው ይገባልም ብሏል።

የፌዴሬሽኑ ሴት አመራሮች ሰብሳቢ ወጣት ማርታ ማሙዬ በበኩሏ የፓርቲዎች ውህደት በሀገሪቱ ተግባራዊ የተደረገውን የፌዴራሊዝም ስርአት በትክክለኛው መንገድ ለማስኬድ ይረዳል ነው ያለችው።

ገዢው ኢህአዴግን በጥምረት የፈጠሩት አራቱ ፓርቲዎችና ሌሎች አጋር የፖለቲካ ድርጅቶች በመወሃድ "የብልፅግና ፓርቲ"  በሚል ስያሜ አንድ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ለመመስረት በሂደት ላይ መሆናቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም