የመድሃኒት ማምረቻ ኢንዱስትሪው የዘርፉን ችግሮች መፍታት የሚችል ባለቤት የለውም ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የመድሃኒት ማምረቻ ኢንዱስትሪው የዘርፉን ችግሮች መፍታት የሚችል ባለቤት የለውም ተባለ
አዲስ አበባ ሰኔ 14/2010 የመድሃኒት ማምረቻ ኢንደስትሪው የዘርፉን ችግሮች መፍታት የሚችል ባለቤት የለውም ሲሉ በመድሃኒትና በህክምና መሳሪያዎች ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት ተናገሩ። የመድሃኒት አቅርቦት ላይ ያሉ ችግሮች፣ የመፍትሄ ሀሳቦችና የባለ ድርሻ አካላት ሚና ላይ በዘርፉ የሚሰሩ የመንግስትና የግል ተቋማት፣ የሙያ ማህበራትና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት የተሳተፉበት ውይይት ዛሬ ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ የተሳተፉ መድሃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ማስመጣትና ማምረት ስራ ላይ የተሰማሩ የግል ተቋማት እንደተናገሩት፤ የመድሃኒትና የህክምና መገልገያዎች ጉዳይ ከሁሉም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባና አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ሆኖም በዘርፉ ያጋጠመው የውጭ ምንዛሬ እጥረትና በወቅቱ ያለማግኘት ችግር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ሆኖ ሳለ ሊፈታ ያልቻለ ከባድ ፈተና መሆኑን ጠቁመዋል። ተቋማቱ እንደገለጹት፤ ከአንድ አመት በላይ የቆየው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር እንዲፈታ በተደጋጋሚ ለባለድርሻ አካላት ጥያቄ ቢቀርብም የችግሩን ስፋትና አሳሳቢነት የሚመጥን ምላሽ የሰጠ ተቋም የለም። ወደ አገሪቱ የሚገቡ ሸቀጦችና የቅንጦት እቃዎች አሁንም በስፋት መገኘታቸውን ገልጸው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ክትትል አናሳ መሆኑንና ቅድሚያ ያለመስጠት ችግሮች መኖራቸው ተገልጿል። “አገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ያለባት ቢሆንም ያለውን የሚሻሙና ለህገ ወጥ ሀብት ማከማቻ ምንጭ የሚያውሉ ወገኖች አሉ'’ ሲሉ ተናግረዋል። በተለያዩ ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ለተያዙ ህሙማን “መድሃኒት የለም'’ ማለት የሚያስከትለውን ስነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ አገናዝቦ በተቆርቋሪነትና በባለቤትነት ስሜት ችግሩን ለመፍታት በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ክፍተቶች መኖራቸውንም አንስተዋል። በኢትዮጵያ ምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን እንዲሁም በባንኮች በኩል ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ያለመኖርና የስነ ምግባር ችግሮች ያሉባቸው ባለሙያዎች በዘርፉ ከሚያጋጥሙ ችግሮች መካከል ተጠቅሷል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየታዩ ያሉ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ችግሮቹን የሚፈቱ ስራዎች ይሰራሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ነው የተናገሩት። ከንግድ ባንክና ከኢትዮጵያ ምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የተገኙ ሀላፊዎችም በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት አስፈላጊ ሰነዶችን አሟልተው ያለማቅረባቸው ቀልጣፋ አገልግሎት የመስጠት ሂደቱን እንደሚፈትነው ገልጸዋል። በውይይቱ ላይ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ችግር ለመፍታት እየተሰራ ያለውን ስራ በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጥ ለብሄራዊ ባንክ ጥሪ የቀረበ ሲሆን በቅርቡ የባንኩ ዋና ሀላፊ የስልጣን ሽግግር የተደረገበት ወቅት በመሆኑ ተገኝተው ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም ተብሏል። የኢትዮጵያ የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሎኮ አብርሃም በበኩላቸው በኤጀንሲው የመድሃኒት አቅርቦትና ስርጭቱን ለማሻሻል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት ኤጀንሲው ማቅረብ የሚችላቸውን መድሃኒቶች በዝርዝር የመለየትና ቀሪዎቹ በግል አቅራቢዎች እንዲቀርቡ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። በመድሃኒት አቅርቦቱ ላይ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግሩ በተጨማሪ የመድሃኒት ስርጭቱ ክፍተቶች ሳቢያ በአንዳንድ ተቋማት መድሃኒቶች የማከማቸት ችግር እንዳለ ተነግሯል። “የመድሃኒት ስርጭቱን በአገር አቀፍ ደረጃ በቅንጅት የሚያስተባብር ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል፤ በዚህም በመድሃኒቶች አቅርቦት ላይ መሻሻሎች ተገኝቷል'' ብለዋል። የመድሃኒት ስርጭት የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ላይ የመቆጣጠሪያ መሳሪያዎችን የመግጠምና መጋዘኖችን በዘመናዊ መልኩ የማደራጀት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል። "በዘርፉ የተሰማራን ሁላችንም ባለድርሻ አካላት ሀላፊነታችንን ያለመወጣት ማለት የበርካቶችን ህይወት የሚያሳጣ ጥፋት መሆኑን በማሰብ ከፍተኛ ጥንቃቄና ርብርብ ልናደርግ ይገባል" ሲሉ ለዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጥሪ አቅርበዋል።