ለተፈራ ኃይሉ ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታ 128 ሚሊየን ብር ተመደበ

77
ኢዜአ ህዳር 18 / 2012 ዓም በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ የሚገኘው የተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ሆስፒታልን ለማስፋፋት የሚውል 128 ሚሊየን ብር መመደቡን የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ገለጸ፡፡ ስራ አስኪያጁ አቶ ፋሲካው ንጋቴ ለኢዜአ እንደተናገሩት ከ20 ዓመታት በፊት የተገነባው ሆስፒታሉ  የዞኑን ህብረተሰብ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ሆኖም አሁን ላይ ከሌሎች ሆስፒታሎች አንጻር ሲታይ የሚያስፈልገውን መስፈርት አሟልቶ ባለመገኘቱ በህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን አውስተዋል። ይህንን በመገንዘብ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ በተያዘው የበጀት ዓመት 128 ሚሊየን ብር በመመደብ የማስፋፊያ ግንባታ ለማከናወን እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ስራ አስኪያጁ እንዳሉት በማስፋፊያ ግንባታውም 420 ካሬ ሜትር  ቦታ ላይ የሚያርፍ ባለ ሶስት ወለል ህንጻ  ነው፤  ወደ አጠቃላይ ሆስፒታል ደረጃ ለማሳደግ ያስችላል። "በሆስፒታሉ  የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በመመደብም የእናቶች እና ህጻናት፣ ድንገተኛ እና የቀዶ ጥገና ህክምናዎችን በበቂ ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጥ ያደርገዋል "ብለዋል፡፡ የማስፋፊያ ግንባታውም በሁለት ዓመት ተኩል ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዷል። ግንባታው በተቀመጠለት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ በሆስፒታሉ በኩል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም