6 የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ለማዞር የሚካሄደው ጨረታ በቅርቡ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
6 የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ለማዞር የሚካሄደው ጨረታ በቅርቡ ይካሄዳል
ኢዜአ ህዳር 17 / 2012 ዓ.ም ስድስት የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ለማዞር የሚካሄደው የመጀመሪያው ዙር ጨረታ በቅርቡ እንደሚካሄድ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ። የኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪ ማሻሻያ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል። በውይይት መክፈቻ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ እንደተናገሩት፤ በመንግስት ባለቤትነት የተያዙ 13 የስኳር ፋብሪካዎች የቴክኒክ፣ የዋጋ፣ የማህበራዊና የአካባቢ ጥበቃ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ጥናቶች በመጪው ታህሳስ እንደሚጠናቀቁ ይጠበቃል። በሚኒስቴሩ በቅርቡ ለሁሉም ክፍት የሆነ ነጻ ጨረታ በስኳር ኢንዱስትሪዎች ላይ ይፋ እንደሚደረግም ተናግረዋል። ስድስት ፋብሪካዎችን ወደ ግል ለማዞር የሚካሄደው የመጀመሪያው ዙር ጨረታ በጥር ወር እንደሚካሄድ ጠቁመዋል። ዶክተር ኢዮብ እንደገለጹት፤ የስኳር ዘርፉ ያሉበትን ማነቆዎች ለመፍታትና አመራሩን ለማጠናከር የሚያስችል ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጅቷል። የረቂቅ ፖሊሲው ዝግጅት አማካሪ የሆኑት ዶክተር ቴዎድሮስ መኮንን በኢትዮጵያ ለስኳር ምርት ተስማሚ አየርና እምቅ ሀብት ቢኖርም የስኳር ምርትና ምርታማነት አነስተኛ መሆኑን አንስተዋል። የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ የስኳር እጥረት ያለበት በመሆኑም ኢትዮጵያ እምቅ ሀብቷን በመጠቀምና ምርታማነቷን በማሳደግ ወደ ውጭ መላክ የሚቻልበት እድል መኖሩንም ጠቁመዋል። ረቂቅ ፖሊሲው የስኳርን ምርታማነት ማሻሻል የሚቻልባቸውን መንገዶች፣ በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት የሚያስችሉ መፍትሄዎችንና በዘርፉ ለመሰማራት አስፈላጊ የሆኑ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን ማካተቱን አብራርተዋል። የህግ ባለሙያና መምህር የሆኑት አቶ ጌታሁን ዋለልኝ የስኳር ኢንዱስትሪው በመንግስት ሲመራ በመቆየቱ የግል ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ የሚያስችል የህግ ማሻሻያ አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። የመንግስትና የግሉን ዘርፍ ያካተተ ተቋም መመስረት አስፈላጊ መሆኑንና በዘርፉ የሚሰማሩ አካላት መብትና ግዴታዎች በረቂቅ አዋጁ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል። የስኳር ኮርፕሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዋዩ ሮባ በበኩላቸው የስኳር ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በተከናወኑ የማሻሻያ ስራዎች ለውጦች እየተገኙ መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ጥቅም ላይ የሚውለው የስኳር መጠን በዓመት ከ600 ሺህ ቶን በላይ ሲሆን ዓመታዊ የስኳር ምርት 266 ሺህ ቶን መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።