የኢትዮጵያዊያን አብሮ የመኖር እሴት ለምን ተሸረሸረ? - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያዊያን አብሮ የመኖር እሴት ለምን ተሸረሸረ?
ኢዜአ ህዳር 17/2012 የኢትዮጵያዊያን አብሮ የመኖር እሴት ለምን ተሸረሸረ? እንዴትስ የአብሮነት እሴቶችን ማዳበር ይቻላል? ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች በብሔርና ሃይማኖት ነክ ምክንያቶች የሰዎች ግጭት፣ መፈናቀልና ሞት መስማት እየተለመደ መጥቷል። ይሁንና ዕኩይ ክስተቶችን መስማት በተበራከተበት በአሁኑ ወቅት ዘጠነኛው 'አገር አቀፍ የአብሮነት ቀን' ከሰሞኑ ሰመራ ከተማ ላይ ተከብሯል። በዓሉን ለማክበር ሰመራ ላይ የከተሙ ታዳሚያን ይህ 'ኢትዮጵያዊያን አብሮ የመኖር ባሕላቸውን አጥተዋል' የሚያሰኝ ድርጊት ለምን ተከሰተ በሚለው ጉዳይ ለኢዜአ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አቶ አብዱልፈታህ አብደላ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ በአገር በቀል እውቀቶቸና እሴቶች ላይ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ከ16 በላይ መጽሃፍትን አበርክተዋል። እናም በኢትዮጵያ አብሮ ለመኖር የሚያግዙ ከ130 በላይ አገር በቀል ስርዓቶች ስለመኖራቸው ይጠቅሳሉ። እነዚህ ባህላዊ ስርዓታት የተፈጠርንባቸው፣ ያደግንባቸው፣ የኖርንባቸውና ማንነታችን የተቀረጸባቸው ፍልስፍናና እሴቶች በዘመናዊ የትምህርት ስርዓቱ ተገፍተዋል፤ ኢትዮጵያዊያንም አብሮ መኖራቸው ተሸርሽሯል ብለውም ያምናሉ። በአፋር ሃገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አባ ወልደአረጋይ ገንዘቤም የኢትዮጵያዊያን አብሮ የመኖር እሴት መሸርሸር ከስነ-ምግባር ጉድለትና በዘመናዊው የትምህርት ስርዓት ያለው የታሪክ መዛባት እንደሆነ ያምናሉ። እየተሸረሸረ የመጣውን የአብሮነት እሴት መመለስ እንደሚቻልም አስተያየት ሰጪዎቹ ይገልጻሉ። አቶ አብዱልፈታህ ዕውቀት ሁልጊዜም ከአካባቢ የሚነጭ መሆኑን አምነው፤ ሌሎች ያደጉ አገራት የአካባቢያቸውን ዕውቀት አገራዊ ከማድረግ አልፈው ዓለም አቀፋዊ ማድረጋቸውን ይናገራሉ። በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ130 በላይ አገር በቀል ዕውቀቶችን ሰብስቦ ወደ ጋራ ስርዓት በማምጣት ቁስና ሃሳብ ከውጭ ከመሸመት ይልቅ መሸጥም እንደሚቻል አብራርተዋል። ለዚህ ደግሞ በምሁራን በውጭ ዕውቀቶች ላይ ብቻ በመንጠልጠል በትርጓሜና አረዳድ ረገድ ክፍተት መኖሩን ጠቁመው፤ ለኢትዮጵያ ዐውዳዊና ተጨባጭ ሁኔታ የማይሆኑትን በቀጥታ መጉረስ የለባቸውም ነው ያሉት። አባ ወልደአረጋይ በበኩላቸው የሃይማኖት አባቶችና የታሪክ ምሁራን ጎጥና ጎሳ እንደሌላቸው ይገልጻሉ። በመሆኑም ሕዝቡ ሃይማኖት አምላኪ በመሆኑ የሃይማኖት አባቶች በአድርባይነት በተቀደደ ቦይ ከመፍሰስ ይልቅ ሃላፊነታቸውን በትክክል መወጣት፤ ምሁራንም እውነተኛውን ታሪክ ማስተማር እንዳለባቸው ተናግረዋል። በሌላ በኩል በአመራርነትና በአብሮነት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ በርካታ መጽሃፍትን የደረሱት ዶክተር እዮብ ማሞ አገራት ለማደግ በቅድሚያ የመተማመን ባህል መፍጠራቸውን ይናገራሉ። በኢትዮጵያም እንደ ዕድር፣ ዕቁብ፣ ሽምግልናና መሰል ባህላዊ ስርዓቶች የሚመሰረቱት በመተማመን መሆኑን ገልጸው፤ የመተማመን ባህል ለአብሮነት እሴት መዳበር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰዋል።