የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ከዩጋንዳ የኢነርጂና ማዕድን ሚኒስትር ጋር ተወያየ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ከዩጋንዳ የኢነርጂና ማዕድን ሚኒስትር ጋር ተወያየ
ኢዜአ፤ ህዳር 17/2012 የኢትዮጵያንና የዩጋንዳን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራው የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ከዩጋንዳ ኢነርጂና ማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሪን ሙሎኒ ጋር ተወያዩ።
የዩጋንዳ ኢነርጂና ማዕድን ሚኒስትሯ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ በሁለትዮሽና በዓለም አቀፍ መድረኮች ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የፐብሊክ ዲፕሎማሲ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት በመግለጽ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ በትብብር ሊሰሩ ከሚችሉባቸው ዘርፎች ኢነርጂና ማዕድን አንዱ መሆኑን አስታውሰው፤ በሁለቱ አገሮች መካከል በዘርፉ የመግባቢያ ስምምነት ለመፈራረም የሰነድ ልውውጥ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በቅርቡ የዩጋንዳ የባለሙያዎች ቡድን በባዮ ፊዩል ዘርፍ ከኢትዮጵያ አቻው ተሞክሮ ለመቅሰም ወደ ኢትዮጵያ ተጉዞ መመለሱንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ዩጋንዳ እና ኢትዮጵያ ትብብራቸውን በተለያዩ ዘርፎች ለማጠናከር እያደረጉ ያለውን እንቅስቃሴ አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ይበልጥ መጠናከር አለበት ብላ ስለምታምን ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ዩጋንዳ መሄዱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ያለባትን የሀይል እጥረት በመቅረፍ ዜጎቿን ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ የኢነርጂ አማራጮችን እየተገበረች መሆኑንም አንስተዋል።
በዘርፉ ሁለቱ አገሮች በትብብር ሊሰሩ የሚችሉባቸው በርካታ እድሎች መኖራቸውንም አንስተው፤ የኢትዮጵያን የሀይል ፍለጎት ትርጉም ባለው መልክ እንደሚቀርፍ የታመነበት ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑንም አብራርተዋል።
ዩጋንዳ የናይል የትብብር ማዕቀፍን በማጽቋም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ምስጋናም አቅርበዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር የአፍሪካና መካከለኛው ጉዳዮች ቋሚ ተጠሪ የሆኑት አምባሳደር ወይንእሸት ታደሰ በበኩላቸው ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ እያደረጉት ያለውን ውይይት በተመለከተ ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የህዳሴ ግድብ ግንባታው እየተፋጠነ መሆኑንና ሶስቱ አገሮች በግድቡ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ ተከታታይ ምክክሮችን አያካሄዱ መሆኑን ገገልጸው፤ግድቡ የሶስቱን አገሮች ፍላጎት ባጣጣመ መልኩ እየተገነባ መሆኑንም አብራርተዋል።
ኢንጂነር አይሪን ሙሎኒ ስለታላቁ የኢትጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስለተደረገላቸው ገለጻና ማብራሪያ አመስግነው የሶስቱን አገሮች ፍለጎት ባማከለ መልኩ ውይይት መደረጉ ጠቀሚ መሆኑን ገልጸዋል።
የአባይ ተፋሰስ ደህንነትን መጠበቅ ወንዙን በዘለቄታዊነት ለመጠቀም ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ ዩጋንዳ የሚጠበቅባትን ለመወጣት እየሰራች መሆኑን መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።