መልካም ስብዕና የተላበሰ ወጣት መፍጠሪያ ቁልፉ ምንድ ነው?

197
ኢዜአ ህዳር 17/2012 መልካም ስብዕና የተላበሰ ወጣት ለመፍጠር ቁልፉ ምን ይሆን? ወጣቶች ለአንድ አገር እድገት ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉትን ያህል የአገርን ህልውናም አደጋ ውስጥ የሚጥሉበት ሁኔታ ይኖራል። በተለይ ያላቸውን ትኩስ ጉልበትና ፍጥነት ለበጎ ነገር ካልተጠቀሙ የሚመጣው ጉዳት ቀላል አይደለም። የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ወጣትነት የሰውነት ጥንካሬ የሚታይበት፣ ለመማርና ለማወቅ ብዙ ጉጉት የሚፈጠርበት፣ ደንቦችና ሕጎች ላይ ማመጽ የሚንጸባረቅበት ነው። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሚታዩ ከማህበረሰቡ ያፈነገጡና ወጣ ያሉ ድርጊቶችን መመልከት እየተለመደ መጥቷል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሥነ ልቦና መምህር ፕሮፌሰር ሀብታሙ ወንድሙ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ወጣቶች መልካም ስብዕና እንዲገነቡ ከቤተሰብ አስተዳደግ ይጀምራል። ቤተሰብ ልጆችን በተለያየ ጉዳዮች ላይ ማሳተፍ ተገቢ እንደሆነም ያስገነዝባሉ። አሁን በአንዳንድ ወጣቶች ዘንድ የሚስተዋለው ሕገ ወጥነት ከአስተዳደግ የሚመነጭ ሊሆን እንደሚችል የጠቆሙት ፕሮፌሰር ሀብታሙ፤ በወላጅና በልጆች መካከል መቀራረብ ካለ አፈንጋጭ ባህሪያት አይከሰቱም። ቁጥጥር አልባ ልቅ የሆነ አስተዳደግ ልጆች ከሕግ ጋር እንዲጋጩ፣ ስርዓት እንዳይጠብቁ፣ ለግብረ ገብነትና ለኃይማኖት ተገዥ እንዳይሆኑ የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል። እንደ ፕሮፌሰር ሀብታሙ ገለጻ፤ ጤናማና መልካም ስብዕና ያላቸው ወጣቶች ራሳቸውን የሚቀበሉ፣ ኃላፊነት የሚወስዱ፣ ምክንያታዊ የሆነ አስተሳሰብ የተላበሱና አዳዲስ ሀሳቦችን ለመማርና ስህተቶችን ለማረም ዝግጁ ናቸው። ወጣቶች ስሜታቸውን በአግባቡ መግለጽ የሚችሉ፣ ለማህበራዊ ፍትህ፣ ለነጻነትና ለእኩልነት የሚቆረቆሩ፣ ሰዎችን የሚወዱና በሰዎች የሚወደዱ እንዲሁም በመልካም ተግባራት ላይ የሚሳተፉ ከሆነ ጥሩ ባህሪ ካላቸው ውስጥ እንደሚመደቡ ገልጸዋል። የማህበራዊ ሥነ ልቦና መምህሩ እንደሚናገሩት፤ መልካም ባህሪ የተላበሰ ወጣት ለማፍራት ቤተሰብ እና ትምህርት ቤቶች መልካም ስብዕና ቀረጻ ላይ በአጽንኦት መስራት ይጠበቅባቸዋል። ''ልጆች ያልሆነ አቅጣጫ ሲከተሉ ማረምና መገሰጽ አስፈላጊ ነው፤ በአንጻሩ ደግሞ ልጆች ጥሩ ባህሪ ሲያሳዩም  እውቅና መስጠትይገባል'' ብለዋል። ''ለወጣቶች ያልተገባ ባህሪ መከሰት የአቻ ግፊት አንዱ ነው'' ያሉት ፕሮፌሰር ሀብታሙ የወጣቶችን መዋያና ተግባር መከታተል ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል። ''ወጣቶች ስለ ወደፊት ህይወታቸው ዋጋ ይሰጣሉ ወይ የሚለው ትልቅ ጉዳይ ነው'' ያሉት ፕሮፌሰር ሀብታሙ፤ ተስፋ መሰነቅ ወጣቶች ወደ ጥፋት እንዳይሄዱ የሚያደርግ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል። ወጣቶች በትንሽ ነገር ወደተስፋ መቁረጥ ከመግባት ይልቅ የተለያዩ አማራጭ መንገዶችን በመፈለግ የወደፊት ተስፋቸውን እንዲያለመልሙ የቤተሰብ እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል።                                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም