ለአፍሪካ የግብርና እድገት ከቻይና ጋር በትብብር መስራት አስፈላጊ ነው -- የቀ/ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ - ኢዜአ አማርኛ
ለአፍሪካ የግብርና እድገት ከቻይና ጋር በትብብር መስራት አስፈላጊ ነው -- የቀ/ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ
ኢዜአ ህዳር 17/2012 ለአፍሪካ የግብርና እድገትና ሽግግር ከቻይና ጋር በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑን የኢትዮጵያ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርና የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ህብረት የቦርድ ሊቀ መንበር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ። ባለፈው ማክሰኞ በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ ከዥንዋ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቦርድ ሊቀ መንበር አቶ ኃይለማርያም እንደተናገሩት፤ አፍሪካ በግብርናው ዘርፍ የምታደርገው ሽግግር የሚያተኩረው ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን አመራረት ወደ ሰፋፊ እርሻ ለማሳደግ ነው። ይህም በግብርናው ትርፍ ምርት በማግኘት ለገበያ በማቅረብ ዘርፉን ተጨማሪ የኢኮኖሚ ምንጭ ለማድረግ ያለመ ነው። በአሁኑ ወቅት መቀመጫውን አፍሪካ ያደረገው የቦርድ ሊቀ መንበር ኃይለማርያም፤ በአፍሪካ የግብርና ሽግግር ማለት ለቀጣዩ የዘርፉ እድገት አስፈላጊውን ግብዓት ማቅረብ ነው። ሽግግሩ ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችን በዲጂታል ቴክኖለጂ በመደገፍና በመጠቀም፤ የግብርና ማቀነባበሪያና ግብርናን መሰረት ያደረገ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚን ከዘመናዊ ግብርና ጋር አቀናጅቶ ማሳለጥ ላይ ያተኮረ ነው ። በቴክኖለጂ የታገዘው ግብርና ደግሞ ምርትን ከማሳደግ ባለፈ በአፍሪካ የሚገኙ ስራ አጥ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ይችላል። "የግብርና ሽግግር ሲባል የተመጣጠነና የምግብ ዋስትና እና ለገበያ የሚሆን ትርፍ ምርት ማምረትን ያጠቃልላል” ብለዋል። ኢትዮጵያ የግብርና ሽግግርን ከጀመረች በኋላ ከቻይና ከግብርና ባለሙያዎች እንዲመጡ ማድረጓን አስታውሰው፤ ባለሙያዎቹ በአገሪቷ የግብርና ኤክስቴንሽን ለማስፋፋት ማስቻሉን ነው የገለጹት። አቶ ኃይለማርያም እንደገለጹት፤ የቻይና ባለሙያዎች ኢትዮጵያውያን የግብርና ባለሙያዎችን በማሰልጠናቸው የእውቀትና ልምድ ልውውጥ ማድረግ ተችሏል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከቻይና በተገኙ ቴክኖለጂዎች ተጠቃሚ መሆኗን የተናገሩት አቶ ኃይለማርያም፤ በጋራ በሚከናወኑ ምርምሮች የሚገኙ ምርጥ ዘሮች ከፍተኛ ምርት እንዲሰጡ ለማድረግ መቻሉን ነው ያመለከቱት። ከዚህ በተጨማሪ የአገሪቷን እድገት ለማስቀጠል የሚያግዝ የገንዘብ ድጋፍ በረጅም ጊዜ ክፍያና በስጦታና ከቻይና መገኘቱን ጠቁመዋል። ቻይና በአጭር ጊዜ ግብርናዋን በማዘመን ህዝቦቿን ተጠቃሚ ያደረገችበትን የሽግግር አሰራር አፍሪካም በራሷ መንገድ መውሰድ እንዳለባት ጠቁመው፤ በዚህም ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በማጣጣም ህዝቦቿን ከረሃብ ልትታደግበት እንደምትችል ጠቅሰዋል። በቻይናና በአፍሪካ መካከል ያለውን ያልተነካ የግብርና ትብብር በማስመልከት "ከቻይና መንግስት፣ የግሉ ዘርፍና ከሲቪል ማህበረሰቡ ጋር በመሆን ግብርናውን ለማዘመን በርካታ ተግባራትን ማከናወን እንችላለን”በማለትም ገልጸዋል። አቶ ኃይለማርያም በመጪው ወር በደቡብ ቻይና ሃኒያን ግዛት በሚካሄደው የቻይና አፍሪካ የግብርና ፎረም ላይ የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ህብረትን (AGRA ) በመምራት ይካፈላሉ።