ለወቅታዊ ችግሮች መፍትሔው በሕዝቦች የአብሮነትና የሠላም እሴቶች ላይ በጋራ መስራት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለወቅታዊ ችግሮች መፍትሔው በሕዝቦች የአብሮነትና የሠላም እሴቶች ላይ በጋራ መስራት ነው
ኢዜአ ህዳር 17/2012 ለወቅታዊ አገራዊ ችግሮች መፍትሔ ለማበጀት በሕዝቦች የአብሮነት፣ የሠላምና የፍቅር እሴቶች ላይ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ። ይህ የተገለጸው ዘጠነኛው አገር አቀፍ የአብሮነት ቀን 'አብሮነት ለአገራችን ሠላም' በሚል መሪ ሃሳብ ከትናንት በስትያ በሰመራ ሲከበር ነው። የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት የሰው ልጅ ህላዌ ከራሱ አልፎ ከአካባቢው ጋር የተሳሰረ መሆኑን፤ አብሮነትም ከራስ አልፎ ከሌሎች ጋር ተሳስቦ የመኖር ተፈጥሯዊ ግዴታ መሆኑን ገልጸዋል። ይሁንና ልዩነትን ባለማክበር፣ እኔ ብቻ በሚል ስግብግብነት፣ የራስን ፍላጎት በሌሎች ላይ የመጫን ፍላጎትና በሌሎች ምክንያቶች አብሮነት እየተሸረሸረ እንደሆነ ተናግረዋል። ኢትዮጵያዊያን በዘመናት አብሮነታቸው የአገርን ሉዓላዊነት በጋራ በማስጠበቅ ቋንቋና ታሪካቸውን ለትውልድ ማሻገር መቻላቸው ከአብሮነት ትሩፋቶች አንዱ መሆኑን በማስታወስ። በመሆኑም ለወቅታዊ ችግሮች መፍትሔው አብሮነት፣ ሠላምና ፍቅር እንዲጠናከር ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በጋራ እንዲሰሩም ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበርን ወክለው የተገኙት አቶ እንድሪያስ ተረፈ በበኩላቸው አብሮነትን የሚያጎለብቱ የባህላዊ እውቀትና ስርዓቶች ላይ ጥናቶች ቢወጡም መሬት ላይ የማውረድ ችገር መኖሩን አንስተዋል። በሕዝቡ ዘንድ ከማንበብ ይልቅ የመናገርና የመስማት ባህል መብለጡን በማንሳትም አገር የሚሰሩ፣ ትውልድ የሚያንጹ የጥናት ውጤቶችን በተግባር ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት። ይህ ደግሞ የሁሉንም ማኅበረሰብ የጋራ ትብብር እንደሚጠይቅ ገልጸዋል። የአፋር ሕዝብና ክልል ነባር ባህላዊ እሴቱ ሳይበረዝ ለትውልድ ያሻገረ የአብሮነት ተምሳሌት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ዑስማን መሃመድ ናቸው። የአብሮነት ቀን በክልሉ መከበሩም ባሕላዊ እሴቶች እንዲጠናከሩና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲዳብር የማድረግ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰዋል። አብሮነትና ሠላም እንዲበለጽግ፣ ኢትዮጵያዊነትም እንዲዳብር የሁሉም ድርሻ መሆኑንም ተናግረዋል።