በፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅ ላይ የህዝብ ውይይት ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅ ላይ የህዝብ ውይይት ተደረገ

ኢዜአ ህዳር 17/2012 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፌደራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅ ላይ የህዝብ ውይይት አደረገ። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅ ላይ የህዝብ ውይይት አድርጓል። አዋጁ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን አለም አቀፍ ስምምነቶችና አለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን የእስረኛ አያያዝ በማጣቀስ የተዘጋጀ ነው ተብሏል። የፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቀ አዋጅ የታራሚዎች አያያዝና ተቋማዊ አደረጃጀትን ጨምሮ ሌሎች ድንጋጌዎችን በመያዝ 72 አንቀጾችን አካቷል። የታራሚዎች የመኖሪያና የመኝታ አገልግሎት፣ የህክምና አገልግሎት፣ የምግብ አቅርቦት፣ የቀለምና የሙያ ስልጠና በረቂቅ አዋጁ ከተቀመጡ አንቀጾች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። አዋጁ የታራሚዎችን የሰብአዊ መብት ክብራቸውን ከሚያዋርዱና ከአድሎአዊ አያያዝ ለመጠበቅ መዘጋጀቱን ረቂቁ ያስረዳል። ቀደም ሲል ሲፈጸም የነበረውን አካላዊና ስነ ልቦናዊ የመብት ጥሰት በማስቀረት የታራሚዎችን አካላዊና በህይወት የመኖር መብት መጠበቅ በማስፈለጉ አዋጁ እንደተዘጋጀም ተቀምጧል። ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው የግል ፍላጎታቸውን መሰረት በማድረግ የትምህርትና ስልጠና መብታቸውን መጠቀም እንደሚችሉም ተደንግጓል። በኢኮኖሚ ተጠቃሚ በማድረግ በኩል በማህበር በማደራጀትና በልማት ስራዎች በማሳተፍ እንዲሁም የስራና የቁጠባ ባህል መልሶ የማቋቋም ስራ እንደሚሰራ ተቀምጧል። የውይይቱ ተሳታፊዎች መስተካከል አለባቸው ያሏቸውን አንቀጾችና ድንጋጌዎች፣ ለትርጉም የተጋለጡ ቃላት፣ ግልጽነት የጎደላቸው አገላለጾችን አንስተዋል። የታራሚዎች የህክምና ምርመራ፣ ታራሚዎችን መልሶ ስለማቋቋም፣ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸውና ከወጡ በኋላ የልማት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ ማመቻቸት ከተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች መካከል ናቸው። ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው በሚያገኙት የሙያ ስልጠና ወደ ማህበረሰቡ ከተቀላቀሉ በኋላ የመቀጠር እክል እንዳያጋጥማቸው ክትትል ለማድረግ የሚያስችል እንዲደረግም አስተያየት ሰጪዎቹ አንስተዋል። የፌደራል ምክትል ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ''በረቂቅ አዋጁ ላይ መስተካከል ያለባቸው ድንጋጌዎችና አንቀጾች ላይ አርትኦት ይደረጋል'' ብለዋል። የማረሚያ ቤቶች ምክትል ኮሚሽነር ያረጋል አደመ በበኩላቸው አዋጁ ሲጸድቅ ታራሚዎችን ከማረምና ማነጽ ባለፈ በጨርቃጨርቅና ሌሎች ስራዎች በመሰማራት ራሳቸውንና አገርን የሚጠቅሙበት አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል። በፍርድ ሂደት ላይ ስለሚታይ መዘግየት፣ በእስረኞች አያያዝ፣ አመክሮና ሌሎች በረቂቀ አዋጁ ቢታዩ ተብለው ከህዝብ በስልክ የቀረቡ ሃሳቦች ተብለው በህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ቀርቧል። በረቂቅ አዋጁ ላይ ዛሬ ከህዝብ የተሰጡ ሃሳቦችና ቀደም ሲል ከተለያዩ አካላት የተሰጡትን ጨምሮ ማስተካከያ በማድረግ እንዲቀርብም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል። የፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅ በተለያየ ጊዜ በውይይት የተነሱ ሃሳቦችን በማካተትና ማስተካከያ ለአፈ ጉባኤው ቀርቦ በምክር ቤቱ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።