በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በሰው ሃይል ቅጥርና በግብአት አቅርቦት የሚታዩ ችግሮች እንዲፈቱ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በሰው ሃይል ቅጥርና በግብአት አቅርቦት የሚታዩ ችግሮች እንዲፈቱ ተጠየቀ
ህዳር 16/2012 በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ከሰው ኃይል ቅጥርና ከግብዓት አቅርቦት ጋር ተያይዘው የሚታዩ ችግሮች እንዲፈቱ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ጠየቁ፡፡ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲው በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ከዩኒቨርሲቲው ማህብረሰብ ጋር ትናንት ውይይት አድርጓል፡፡ የውይይቱ ተሳፊዎች እንዳሉት በዩኒቨርሲቲው ከሰው ኃይል ቅጥርና ከደረጃ እድገት እንዲሁም ከግብዓት አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮች ይታያሉ ። በተለይም ከቤተ መጽሐፍት፡ ከቤተ ሙከራና ከመማሪያ ክፍሎች ጋር ተያይዘው የሚታዩት ችግሮች በፍጥነት እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል ። ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ለሚያካሔዳቸው የምርምር ስራዎች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግ ተሳታፊዎቹ ጠቁመዋል ። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ዶክተር ጀንበሩ አለሙ በሰጡት አስተያየት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የመማር ማስተማሩን ሂደት የሚያሳልጡ ግብዓቶች መሟላት አለባቸው ብለዋል። በተለይም በዩኒቨርሲቲው ከግንባታ መዘግየት ጋር ተያይዞ የሚስተዋለው የክፍሎች ጥበት፡ የመምህራን መኖሪያና የቢሮዎች ችግር እንዲፈቱ ጠይቀዋል ። እንዲሁም ከግብዓት አቅርቦት ጋር ተያይዞ በቤተ መጽሐፍት፡በቤተ ሙከራና በሌሎችም ዘርፎች የሚስተዋሉ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የታለመለትን የመማር ማስተማርና የምርምር ሂደት ለማሳለጥ የሚያደርገውን ጥረት ለማጠናከር በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶች መሟላት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ባሉት ክፍት የስራ ቦታዎች ላይ የሰው ኃይል ለማሟላት ማስታወቂያዎች ከወጡ በኋላ ውጤቱ የማይገለጹበት ሁኔታ መኖሩን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ መምህር ቾል ኬት ናቸው፡፡ ይህም በዩኒቨርሲቲው ማህብረሰብ ውስጥ ቅሬታን እየፈጠረ መሆኑን በመግለጽ በቀጣይ ይህ ችግር በትኩረት ሊፈታ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ዶክተር ቤል ቢቾክ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታቱ ረገድ የዩኒቨርሲቲው ቦርድ የሚያደርገው ጥረት በተለይም በየደረጃው የሚገኙ ሰራተኞችን ከማወያየት አኳያ ክፍተቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የመማር ማስተማርም ሆነ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት በኩል የሚሰሩ ስራዎች ቢኖሩም ለችግሮቹ መፍትሄ በመስጠት በኩል ግን ክፍተት እንዳለ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያለውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት አጠናክሮ ለማስቀጠል ቦርዱ የሚያደርገውን ክትትልን ቁጥጥር ማጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ዬኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማሩን ሂደት ሰላማዊ ለማድረግ ባለው ውስን ሀብት በትኩረት እየሰራ ነው፡፡ ይህንን ለማጠናከር በተለይም ከመሰረተ ልማትና ከግብዓት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከሰው ኃይል ቅጥር ጋር ተያይዞ የተነሱ ጥያቄዎችን በተመለከተ እስከ አሁን ድረስ ምንም አይነት ቅሬታ አለመድረሱንና ችግሮች ካሉም በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ረሺድ ሙሐመድ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው ማህብረሰብ በግቢው ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር እያደረጉት ያለውን ጥረት ማጠናከር አለባቸው ብለዋል፡፡ ቦርዱም በዩኒቨርሲቲው ማህብረሰብ የተነሱ ችግሮችን ለመፍታት ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር በመሆን በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ ተምሳሌት መሆኑን በመጠቆም በቀጣይም ይህንን እሴት ማጎልበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞችና ሌሎች አካላት ታድመውበታል፡፡