በአገሪቱ ስኳር ፖሊሲና የዘርፉን አሰራር ለመከታተል በተዘጋጀው መመሪያ ላይ ምክክር ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
በአገሪቱ ስኳር ፖሊሲና የዘርፉን አሰራር ለመከታተል በተዘጋጀው መመሪያ ላይ ምክክር ይካሄዳል

ህዳር 16/2012 የኢትዮጵያን የስኳር ኢንዱስትሪ በአግባቡ በመምራት ልማቱን ማፋጠን ይቻል ዘንድ በተረቀቀው የአገሪቱ ስኳር ፖሊሲና የዘርፉን አሰራር ለመከታተል በተዘጋጀው መመሪያ ላይ የሚነጋገር የምክክር መድረክ ነገ እንደሚካሄድ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ። በምክክር መድረኩ በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ዙሪያ እየተከናወነ ያለው ማሻሻያ (ሪፎርም) ላይም ውይይት ይደረጋል ተብሏል። ሚኒስቴሩ ለኢዜአ እንዳስታወቀው በምክክር መድረኩ ላይ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች፣ የዘርፉ ሙያተኞች፣ የህግ ሰዎችና የምርምር ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ የባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ተሳታፊዎቹም የስኳር ፖሊሲንና ኢንዱስትሪው የሚመራበትን መመሪያ ይገመግማሉ። በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የሚመራው መንግስት እየወሰዳቸው ካሉት እርምጃዎች መካከል የተለያዩ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ለግል ባለሃብቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የመሸጥ ሃሳብ አንዱ ነው። ወደግል ዘርፍ እንዲዘዋወሩ ከተወሰኑት የመንግስት ልማት ድርጅቶች መካከል የስኳር ፋብሪካዎች ይገኙበታል። ሚኒስቴሩ የስኳር ፋብሪካዎችን አዋጅ በማዘጋጀት ላይ ሲሆን አዋጁ የሚዘጋጀው በስኳር የማምረት፣ የመሸጥ፣ ወደ ሃገር ዉስጥ የሚገቡና ወደ ዉጭ የሚላኩ የስኳር ምርትን በአግባቡ ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር እንዲቻል ነዉ፡፡