ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ ግብረኃይል ተቋቁሞ ወደሥራ ተገብቷል

ኢዜአ ህዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም በደቡብ ክልል የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ ለመሰብሰብ በሚደረገው ጥረት በየደረጃው ያሉ ሁሉም አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ተጠየቀ። በክልሉ የሰብል ስብሰባ ሥራውን በተደራጀ መልኩ የሚያስተባብር ግበረ-ኃይል ተቋቁሞ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ሥራ መገባቱ ተገልጿል። የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይጎዳ ለማሰባሰብ እየተከናወነ ያለውን ሥራ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ የቢሮው ምክትልና የእርሻ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው እንደገለጹት በ2011/12 የመኸር ምርት ዘመን በክልሉ 1 ሚሊዮን 11 ሺህ ሄክታር መሬት በሰብል ተሸፍኗል፡፡ በምርት ዘመኑ የግብአት አቅርቦትና አጠቃቀምን በማሻሻል እንዲሁም በክላስተርና በኩታ ገጠም ማሳ በማልማት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ የመኸሩ የዝናብ ሁኔታ ለምርታማነት መጨመር አስተዋጽኦ ማድረጉን የገለጹት አቶ ዳንኤል፣ "በተደረገ የቁም ምርት ግምት ዘንድሮ የሚሰበሰበው የሰብል ምርት መጠን የተሻለ እንደሚሆን ተረጋግጧል"ብለዋል። እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገለጻ በመኸሩ ከለማው መሬት ከ98 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰብል ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል ፡፡ "በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት እየጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሚጠበቀው ምርት ላይ ሥጋት ደቅኗል" ያሉት አቶ ዳንኤል፣ ባለድርሻ አካላትና አርሶ አደሩን በማስተባበር የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ ማንሳት እንደሚገባ አመልክተዋል። ምርቱን በማሽነሪዎች ለመሰብሰብ በተሰጠው ትኩረት በክልሉ ከ90 በላይ ኮምባይነሮች ቢኖሩም ዝናቡ ማሽኖቹን ለማንቀሳቀስ እንቅፋት እንደሆነ ተናግረዋል። የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ ለመሰብሰብ በሚደረገው ጥረት በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት የሰው ኃይሉን አስተባብረው ሰብልን መሰብሰብ የተሸለ አማራጭ መሆኑንም አቶ ዳንኤል አመልክተዋል፡፡ ኃላፊው የአየር ትንበያ ሁኔታን ዋቢ አድርገው እንደገለጹት በቀጣይ ተከታታይ 10 ቀናት የሚጥለው የዝናብ መጠን እየጨመረ ይሄዳል። በክልሉ ከዛሬ ጀምሮ ባሉት ቀናት ሁሉም አካላት ሰብልን ፈጥኖ ለመሰብሰብ ከፍተኛ ርብርብ እንደሚያደርግም አመልክተዋል። እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገለጻ እስካሁን ድረስ ሰብል ከደረሰባቸው የክልሉ አካባቢዎች በ180 ሺህ ሄክታር ላይ የነበረ ሰብል ተሰብስቧል፡፡ በማዕከላዊ የክልሉ አካባቢዎች ምርቱ ሙሉ በሙሉ የደረሰ በመሆኑ በነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ በክልሉ ተቀዛቅዞ የነበረውን የአርሶና አርብቶ አደር አካባቢዎች የልማት ሥራ ለማነቃቃት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ሥራዎች መሰራታቸውን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የገጠር ህዝብ አደረጃጀትና ተሳትፎ አማካሪ አቶ አክሊሉ ታደሰ ናቸው ፡፡ "በመኸር ምርት አሰባሰብ ላይ ያጋጠመውን ወቅታዊ ችግር ለመከላከል ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አስተባብሮ በምርት ስብሰባ ሥራ ላይ ማሰማራት ይገባል" ያሉት አቶ አክሊሉ፣ ለእዚህም በአሁኑ ወቅት ከክልል ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ ግብረ-ኃይል መዋቀሩን ተናግረዋል፡፡ ግብረኃይሉም ከዛሬ ጀምሮ እስከ 10 ቀንት በሚቆየው ምርት የማሰባሰብ እንቅሰቃሴ ስራውን  እንደሚያስተባብር አመልክተዋል፡፡ እንደ አቶ አክሊሉ ገለጻ በሰብል ስብሰባው ሥራ ሴቶችና ወጣቶች፣ ተማሪዎች፣ መምህራን እና የመንግስት ሠራተኞች ከአርሶ አደሩ ጋር በመተባበር ይሳተፋሉ፡፡ በክልል ደረጃ የተዋቀረው ግብረኃይል በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የሚመራ መሆኑንም አመልክተዋል። የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተሰማ ዲማ በበኩላቸው ተማሪዎችና መምህራን እንዲሳተፉ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይተው ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ ለእዚህ ሰብል በደረሰባቸው የክልሉ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከዛሬ ጀምሮ እስከ አርብ ድረስ ዝግ እንደሚሆኑም አመልክተዌል ፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም