በኢትዮጵያና ጃፓን መንግስታት መካከል የ2 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ብድር ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና ጃፓን መንግስታት መካከል የ2 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ብድር ስምምነት ተፈረመ
ኢዜአ/ ህዳር 16 /2012 በኢትዮጵያና ጃፓን መንግስታት መካከል የ2 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የብድር ስምምነት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተፈረመ። ገንዘቡ ለጅማ - ጭዳ የመንገድ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል ነው ተብሏል። ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አድማሱ ነበበና በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳይሱኬ ማትሱናጋ ናቸው። ሚኒስትር ዴኤታው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የብድር ስምምነቱ 80 ኪሎ ሜትር ለሚሸፍነው የጅማ - ጭዳ የመንገድ ፕሮጀክት የአስፓልት ኮንግክሪት ግንባታ ሥራ የሚውል ነው። የመንገድ ግንባታው ጅማና አካባቢዋን በማገናኘት የግብርና ምርቶችን ከአንዱ ስፍራ ወደሌላው በቀላሉ ለማጓጓዝ ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። አካባቢው ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና የሚመረትበት በመሆኑ ምርቱን በቀላሉ ለውጭ ገበያ ለማቅረብም መንገዱን ማሻሻል ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም አመልክተዋል። ጃፓን የኢትዮጵያን የመሰረተ ልማት ግንባታ ለማፋጠን እያደረገችው ላለው ድጋፍ ሚኒስትር ዲኤታው ምስጋና አቅርበው፤ የሁለቱ ሀገሮች ትብብር እንደሚቀጥልም ተስፋቸውን ገልፀዋል። በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳይሱኬ ማትሱናጋ በበኩላቸው፤ ጃፓን የኢትዮጵያ የልማት አጋር እንደመሆኗ የሀገሪቱን መሰረተ ልማት ለማሻሻል ለሚካሄዱ ተግባራት ቅድሚያ በመስጠት ትደግፋለች ብለዋል። አምባሳደሩ አክለውም "የጅማ - ጭዳ 80 ኪሎ ሜትር የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ማሻሻያ ፕሮጀክትም ለኢትዮጵያ መሰረተ ልማት ግንባታ የምናደርገው ድጋፍ አንዱ አካል ነው" ሲሉም ገልፀዋል። መንገዱ የሚገኝበት ስፍራ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና የሚመረትበት በመሆኑ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ እጥረቷን ለመቀነስ ትጠቀምበታለች ብለዋል። ዛሬ የተፈረመው የመንገድ ማሻሻያ ፕሮጀክት ስምምነት በቅርቡ ወደተግባር ይለወጣል ሲሉም ገልፀዋል። ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንደሚጠናቀቅም ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል። በኢትዮጵያና ጃፓን መካከል ያለው የቆየ ወዳጅነት የበለጠ እንዲጎለበት የዛሬው ስምምነት አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት አምባሳደሩ። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በበሉላቸው የጃፓን መንግስት ያደረገው የብድር አቅርቦት ስትራቴጂክ ለሆነው የጅማ - ጭዳ የመንገድ ፕሮጀክት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።