ቀጥታ፡

የየመን መንግስት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ነው --- አምባሳደር ያህያ አልአርያኒ

ኢዜአ ህዳር 16/12 ዓ/ም- በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያውን ስደተኞች ወደ አገራቸው በሰላም እንዲመለሱ መንግስታቸው ድጋፍ እያደረገ መሆኑን በኢትዮጵያ የየመን አምባሳደር አምባሳደር ያህያ አልአርያኒ ገለጹ። በኢትዮጵያና የመን የሁለትዮሽ ግንኙነትና በየመን ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጉዳይ በኢትዮጵያ የየመን አምባሳደር ያህያ አልአርያኒን ኢዜአ አነጋግሯቸዋል። አምባሳደር ያህያ ''የየመን መንግስት ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በተመለከተ ወደ ኢትዮጵያ በሰላም እንዲመለሱ አስፈላጊው ጥረት እያደረገ እንደሆነና ዜጎችም ወደ አገራቸው እየተመለሱ ነው'' ብለዋል። ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) እና ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከ800 በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል። ሌሎች ኢትዮጵያውን ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አሁን ያለው ትብብር ወደፊትም በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥልና ዜጎቹ ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መንግስታቸው የሚችለውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያውን ስደተኞች ወደአገራቸው የሚመለሱባቸውን የተለያዩ አማራጮች እንዲፈልግ ከኢትዮጵያ በኩል ጥያቄ እንደቀረበ ገልጸዋል። በዚህም መሰረት የየመን መንግስት ለአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥያቄውን እንዳቀረበና የየመን የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ ጉዳዩን እንዲከታተልና ሌሎች አማራጮች ለማየት ጥረት እያደረገ መሆኑን ነው አምባሳደር ያህያ ያስረዱት። ''በየመን ያለው ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ የምናደርገው ጥረት ላይ ጫና እየፈጠረ ነው'' ያሉት አምባሳደሩ፤ በአገሪቷ ያለው ችግር በሚፈለገው ደረጃ ስራዎችን ማከናወን እንዳላስቻለ ገልጸዋል። በየመን በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያን ስደተኞች የህክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነና ለዜጎቹ አስፈላጊው ጥንቃቄና እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደሆነ አመልክተዋል። የየመን መንግስት ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያውያን እንግልት እንዳይደርስባቸው እየሰራ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ''ኢትዮጵያውያን የየመን ስደተኞችን በር ከፍተው እንደተቀበሉት እኛም ለኢትዮጵያውን ስደተኞች አስፈላጊውን ድጋፍ እናደጋለን'' ብለዋል። ኢትዮጵያና የመን በደም የተሳሰረና ለዘመናት የቆየ ትስስር እንዳላቸውና የትኛውም አይነት ችግር የሁለቱን አገሮች ህዝቦች እንደማይለያያቸው ገልጸዋል። በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ አቋሞችን እያንጸባረቁ እንደሆነና በዚህም ረገድ መልካም የሚባል ትብብር እንዳላቸው ገልጸዋል። አገሮቹ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዲጠናከርም መንግስታቸው እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ ያለው ለውጥ መልካም የሚባልና ለኢትዮጵያ የወደፊት ብሩህ ተስፋ ያለው ሂደት እንደሆነ ነው አምባሳደር ያህያ ያስረዱት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሁን በየመን ያለውን አለመረጋጋትና ጦርነት የመኖች በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ አሁን በየመን ካለው ወቅታዊ መንግስት ጎን ሆና ለምታደርገው ድጋፍና የመኖች ችግራቸውን በውይይት እንዲፈቱ ለምታደርገው ጥረት አምባሳደሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም