ቤጉህዴፓ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ለመዋሃድ ወሰነ

87
ኢዜአ ህዳር 15 /2012ዓ.ም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/ቤጉህዴፓ አባላት ዛሬ ባካሄዱት አስቸኳይ ጉባኤ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ለመዋሃድ ወሰኑ። የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አድጎ አምሳያ እንደተናገሩት የፓርቲው አባላት በኢህአዴግ ድርጅት አባል ባለመሆናቸው በሃገራዊ ጉዳዮችም በባለቤትነት ሳይሳተፉ ቆይዋል። ረጅም ዓመታት ሲያነሱት የቆየው የውህደት ጥያቄ በኢህአዴግ የተሳሳቱ እሳቤዎች ተቀባይነት ሳያገኝ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ አሁን ጥያቄው ተቀባይነት ማግኘቱን ጠቁመው በአዲስ መልክ የሚፈጠረው ሃገራዊ የብልጽግና ፓርቲ ውስጥ የመሳተፍ እድል እንደተመቻቸም አስታውቀዋል፡፡ ውህደቱ የፌዴራል ስርዓትን በማፍረስ በአሃዳዊ ስርዓት የሚተካ ነው በሚል የሚነሳው ሃሳብ የተሳሳተና ከእውነት ጋራ የሚጋጭ አቋም የሚያራምዱ ወገኖች እሳቤ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ “የብልጽግና ፓርቲ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ በማጥበቅ ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትን የሚፈጥር እንደሆነ አመልክተው የክልሉ ህዝቦች በሃገራዊ ጉዳዮች በጋራ ለመወሰን የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል” ብለዋል፡፡ “የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው ከ20 ዓመታት በላይ የተመራንበት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ህዝባችን ያልተወያየበትና እና የላመነበት ነበር ሲሉ” ተናግረዋል፡፡ ፓርቲው አዲስ የጀመረው የብልጽግና መንገድ ግን ሁሉንም አሳታፊ መሆኑን ጠቅሰው የውህደት እንቅስቃሴ ከተጀመረ ጀምሮ ከክልል አመራር እስከ ታችኛው ማህበረሰብ ለማሳተፍ የተደረገውን ጥረት ጠቅሰዋል፡፡ “ይህም የብልጽግና ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ አካሄድን እየተከተለ መሆኑን ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡ ከሌሎች የሃገሪቱ ህዝቦች ጋር በመፈቃቀድና በመከባበር መርህ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን ትግል እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡ ክልሉ በርካታ የተፈጥሮ ጻጋዎች ቢኖሩትም ህብረተሰቡ በድህነት ውስጥ መቆየቱ በእጅጉ የሚያስቆጭ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ አዲሱ የብልጽግና ፓርቲ በአባልነት እንዲሳተፉ የከፈተው በር ህዝቡን ከድህነት ለማውጣት በላቀ ድል ለማጀብ የሚያስችል እንደሆነ አቶ አሻድሊ አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም ውህደቱን ተከትሎ ከተፈጠረው የብልጽግና ፓርቲ ጋር ቤጉህዴፓ መቀላቀሉ በህዝቡም ሆነ በአጠቃላይ በፌዴራል ስርዓቱ ላይ ምንም የሚያሳድረው ተጽእኖ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ አንዳንድ የፓርቲው አባላት በበኩላቸው የህብረተሰቡ ማንነት እና ከሌሎች ህዝቦች እኩል ተጠቃሚነት እስካለው ድረስ የውህደቱን አስፈላጊነት የሚያምኑበት እንደሆነ ተናግረው ለፓርቲው ውጤታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል። በአስቸኳይ ጉባኤው የተሳተፉ 240 የፓርቲው አባላት የቤጉህዴፓ ወደ ብልጽግና ሃገራዊ ፓርቲ መዋሃድን በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም