ስደተኞች ከሊቢያ ተነስተው ሩዋንዳ መድረሳቸው ተነገረ - ኢዜአ አማርኛ
ስደተኞች ከሊቢያ ተነስተው ሩዋንዳ መድረሳቸው ተነገረ
ኢዜአ፤ ህዳር 15/2012 ሊቢያ ውስጥ በስደተኛ ማቆያ ጣቢያ የነበሩ በሶስተኛ ዙር መልሶ ለማቋቋም ፕሮግራም ተይዞላቸው የነበሩ በርካታ ስደተኞች ሩዋንዳ መግባታቸው ተገልጿል። የሩዋንዳ መንግስት የኤርትራ እና ሶማሊያ ዜግነት አላቸው የተባሉ ስደተኞችን የሚያሳይ ምስል በትዊተር ገፁ ላይ ማጋራቱንም የቢቢሲ መረጃ ጠቁሟል፡፡ የሩዋንዳ አደጋ ጊዜ አስተዳደር ሚኒስቴር በትዊተር ገፁ ላይ በሊቢያ ኢቲኤም ስር የነበሩ 116 ስደተኞች እና ጥገኝነት ፈላጊ የሶስተኛ ዙር አባላት ወደ ሩዋንዳ በሰላም ደርሰዋል ሲል ገልጿል፡፡ መስሪያ ቤቱ በማከልም 189 የሚሆኑት ጥገኝነት ፈላጊ ስደተኞች ጋሸራ በሚገኘው የመተላለፊያ ማዕከል ስር ይስተናገዳሉ ብሏል፡፡ በቦታው የስደተኞች ማስተባበሪያ ቡድን መስከረም እና ጥቅምት ወር ላይ ሩዋንዳ የገቡ 189 ስደተኞችን በኪጋሊ አየር መንገድ አማካኝነት ከዋና ከተማዋ በ40 ኪሎ ሜትር ወይም 24 ማይል ርቀት ላይ በምትገኘው የጋሸራ መተላለፊያ ማዕከል አጓጉዞ ማስፈሩን ዘገባው ያሳያል፡፡ የመልሶ ሰፈራ ማቋቋም ፕሮግራሙ በሩዋንዳ መንግስት፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ እና በአፍሪካ ህብረት መካከል በተደረገ ስምምነት መሆኑንም በዘገባው ተገልጿል፡፡ መዳረሻቸውን ወደ አውሮፓ ለማድረግ በሊቢያ በኩል ሲጓዙ በቁጥጥር ስር ከዋሉ 5ሺ ህገ-ወጥ ስደተኞች መካከል 4ሺ የሚሆኑትን መልሶ ለማቋቋም ከስምምነት ላይ መደረሱንም የቢቢሲ ዘገባ ያሳያል።