ቀጥታ፡

በወረዳው ቀይ ሽንኩርት የሚያለሙ አርሶ አደሮች ከምርታቸው እስክ 25 በመቶ የሚሆነው ለደላላ ጥቅም እንደሚውል ገለጹ

(ኢዜአ) ህዳር 15 /2012ዓ.ም በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ ቀይ ሽንኩርት በመስኖ የሚያለሙ አርሶ አደሮች ከምርታቸው እስክ 25 በመቶ የሚሆነው ለደላላ ጥቅም ስለሚውል መንግስት ገበያ እንዲፈልግላቸው ጠየቁ። የባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ የመስኖ ልማት ንቅናቄ ሥራ በወረዳው አንዳሳ ቀበሌ ዛሬ ተጀምሯል። በወረዳው መስኖን በመጠቀም ቀይ ሽንኩረት የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለጹት ከሚያመርቱት ምርት እስከ 25 በመቶ የሚሆነው የሚውለው ለደላላ ጥቅም ነው። አርሶ አደር ተውልኝ ደሴ እንዳሉት በየዓመቱ ግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ቀይ ሽንኩርት በመስኖ ቢያለሙም የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም። በየዓመቱ ከ80 ኩንታል በላይ ቀይ ሽንኩርት በመስኖ ልማት ቢያመርቱም ምርታቸውን በአግባቡ ሽጠው ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል የገበያ ትስስር ችግር አለባቸው። ምርታቸውን በተገቢ ዋጋ ለተጠቃሚዎች ለመሸጥ የመሸጫ ቦታ እንዲመቻችላቸው ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር ሆነው ቢጠይቁም ምላሽ ባለማግኘታቸው በደላሎች አማካኝነት ለነጋዴዎች እየሸጡ መሆናቸውን ገልጸዋል። "አርሶ አደሩ ይህንን የሚያደርገው አማራጪ ስላጣና ሽንኩርት በባህሪው ፈጥኖ የሚበላሽ በመሆኑ ተጎድቶም ቢሆን መሸጥ ስላላበት ነው" ብለዋል። በባለፈው ዓመት ካመረቱት 95 ኩንታል ምርት 120 ሺህ ብር ለማግኘት አቅደው እንደነበር ጠቁመው በደላላ አማካኝነት በመጣ ነጋዴ ከማሳቸው ላይ 90 ሺህ ብር ለመሸጥ መገደዳቸውን በማሳያነት ገልጸዋል። መንግስት በመስኖ የሚለሙ ምርቶች መጠናቸው እንዲጨምር ብቻ ሳይሆን በገበያው አርሶ አደሩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ጠይቀዋል። "ባመረትነው ምርት ላይ እኛ ተደራድረን ሳይሆን በደላሎች መልካም ፈቃድ ላይ ተመስርተን ነው የምንሸጠው" ያሉት ደግሞ የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መኳንት አንዳርግ ናቸው። በየአመቱ አንድ ሄክታር መሬት ላይ ቀይ ሽንኩርት በመስኖ እያለሙ በምርት ደረጃ የሚጠብቁትን እያገኙ ቢሆንም ከተጠቃሚነት አንጻር ለደላላ ሰለባ መሆናቸውን ይናገራሉ። በባለፈው ዓመት ያመረቱት 98 ኩንታል ሽንኩርት በወቅቱ ገበያ 140 ሺህ ብር ቢገመትም እርሳቸው መሸጥ የቻሉት 98 ሺህ ብር ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። ለእዚህም ወደገበያ ወስዶ ምርታቸውን ለመሸጥ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ አለመኖሩን በማሳያነት ጠቅሰዋል። አርሶ አደር መኳንነት እንዳሉት ዘንድሮ በአንድ ሄክታር መሬት ከ140 ኩንታል በላይ ምርት በማምረት 170 ሺህ ብር ለማግኘት አቅደው እየሰሩ ነው። የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት ለህገወጥ ደላሎች መፈትሄ እንዲፈልግላቸው ነው የጠየቁት። የወረዳው ግብርና ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይታያው ታረቀኝ በበኩላቸው በወረዳው 6 ሺህ ስድስት ሄክታር መሬት በሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመንና ሌሎችም አትክልትና ፍራፍሬዎች በመስኖ ለማልማት ታቅዶ ወደስራ መገባቱን ጠቁመዋል። በመስኖ ልማቱ በሄክታር በአማካኝ 178 ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው"የአርሶ አደሩን ቅሬታ ለመፍታትና የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየሰራን ነው" ብለዋል። ለአርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ለመፍጠር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደሥራ መገባቱን የገለጹት አቶ ይታያው፣ "የመስኖ ሕብረት ስራ ማህበራትን በማቋቋም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እንዲሆን ይሰራል" ብለዋል። ህገወጥ ደላሎች የአርሶ አደሩ ልጆች መሆናቸውን የገለጹት አቶ ይታየው፣ አርሶ አደሮች እነዚህን ደላሎች በመቃወምና ለሚመለከተው አካል በማጋለጥ በኩል ያለባቸውን ውስንነት እንዲያስተካክሉ ጠይቀዋል። የአርሶ አደሩን የገበያ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ምርቱን በኩታ ገጠም እንዲያመርት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በንቅናቄው ላይ የተገኙት የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጥሩነህ ሞሴ ናቸው። በዚህ ዓመት በዞኑ በመስኖ ከሚለማው 30 ሺህ ሄክታር መሬት ግማሹን በኩታ ገጠም ለማልማት ታቅዶ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል። የኩታ ገጠም ልማቱ ለአርሶ አደሩ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና የአርሶ አደሩን ምርት የሚረከቡ ዩኒየኖች በአንድ ጊዜ ምርታቸውን ለማንሳት እንዲችሉ ታስቦ መሆኑን ገልጸዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም