በፕሪሚየር ሊጉ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግርን ለመፍታት የደጋፊ ማህበራት ጥምርት እየተቋቋመ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በፕሪሚየር ሊጉ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግርን ለመፍታት የደጋፊ ማህበራት ጥምርት እየተቋቋመ ነው
ኢዜአ ህዳር 15/2012 በእግር ኳስ ጨዋታ ላይ የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግርን ለመፍታት ያለመ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ደጋፊ ማህበራት ጥምረት እየተቋቋመ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር በተለይም ባለፈው ዓመት በእግር ኳሱ የብሔርና የፖለቲካ አመለካከቶች ማንጸባረቂያ እየሆነ መጥቷል። ይሄን እየተባበሰ የመጣውን የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት በዘንድሮው ዓመት እንዳይደገም የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ። ለዚህም የክለብ ደጋፊዎች ማህበር ጥምርትን ለመመስርት የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክለቦች ደጋፊ ማህበራት ተወካዮች ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል። ጥምረቱ ከ16 ክለቦች ደጋፊዎች የተውጣጡ ሆነው ከእያንዳንዳቸው ሦስት ሦስት ባጠቃላይ 48 አባላት ያለው የደጋፊዎች ማህበራት ጥምርት እንደሚሆን ታውቋል። የእግር ኳሱ ጨዋታ ከፖለቲካና ከብሔር ተኮር አመለካከት የፀዳ እንዲሆን ያለመው ይኸው ጥምረት ከሁሉም ክለቦች የተውጣጡ 16 የስራ አስፈጻሚ አባላት ያለው እንደሆነም ተጠቅሷል። የደጋፊ ማህበራቱ ጥምረትም በአንድ ወር ውስጥ እውን እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን ለዚህም የተለያዩ ውይይቶችን ማካሄዱንና ሰነዶችን የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተገልጿል። በደጋፊዎች መካከል እርስ በርስ መተዋወቅ እንዲፈጠር፣ ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት ስልጠናዎችን መስጠት፣ ክለቦች ከተረጅነት ተላቀው በፋይናንስ እንዲጠናከሩ ደጋፊዎች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉና የተሞክሮ ልውውጥ እንዲካሄድ ማድረግ ጥምረቱ ካነገባቸው ዓላማዎች ተጠቃሽ ነው። እንዲሁም የእግር ኳስ ጨዋታዎች ከማንኛውም የፖለቲካና ብሔር ተኮር አመለካከትና ወገንተኝነት ተላቆ እግር ኳሳዊ ባህሪ እንዲላበስም በጋራ እንደሚሰራ ተገልጿል። የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሲካሄዱ እንግዳው ክለብና ደጋፊዎቹ ደህንነታቸው ተጠብቆና መብታቸው ተከብሮላቸው ያለስጋት ጨዋታው እንዲከናወን ጥምረቱ ከባለ ሜዳው ክለብ ጋር እንደሚሰራም ተነግሯል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ እንዳሉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ በጸጥታ ችግር ውስጥ ወድቋል፤ በዚህም የተነሳ ስጋቱ ከክለቦች አልፎ ለአገር እየተረፈ ነው። በዚህ ወቅት የክለቦች ደጋፊ ማህበራት የጸጥታውን ችግር ለመፍታት በጋራ ለመስራት በመስማማታቸው ጥሩ ጅማሮ እንደሆነ ገልጸዋል። ይህም ክለቦቹ የጸጥታ ችግሩን ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ስለሆነም ደጋፊዎች የእግር ኳሱን ሰላም የሚነሳ ኃይልን በማጋለጥ ለህግ አሳልፎ ለመስጠት መስራት እንደሚገባ ተናግርዋል። የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታም ነገ በፋሲል ከነማና በመቀሌ 70 እንደርታ መካከል በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል። በመቀጠልም የ2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በመጪው እሁድ ህዳር 21 የሚጀምር መሆኑ ይታወቃል። እነዚህ ጨዋታዎች ዓመቱን ሙሉ በሰላምና በስፖርታዊ ጨዋነት እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።