ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የኢትዮጵያ ሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የ2010 ዓ.ም አሸናፊ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የኢትዮጵያ ሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የ2010 ዓ.ም አሸናፊ ሆነ
አዲስ አበባ ሰኔ 14/2010 ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ሆነ። በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ዛሬ በተከናወነው ሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ በሶስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ጌታዘሩ ስፖርት ክለብን ሶስት ለዜሮ በማሸነፍ ሻምፒዮናነቱን አረጋግጧል። ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የኢትዮጵያ ሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግን ለአራተኛ ተከታታይ ዓመት በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ሁለቱ ቡድኖች ካላቸው ልምድ አንጻር ተመጣጣኝ ፉክክር ይታያል ተብሎ ቢጠበቅም በጨዋታው ላይ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የበላይነት ነበረው። በውጤቱ መሰረትም ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በ15 ነጥብ አንደኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ ውሃ ስራዎች በ12 ነጥብ ሁለተኛ እንዲሁም ጌታዘሩ ስፖርት ክለብ በ9 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል። ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡት ተወዳዳሪዎች የሜዳሊያ ሽልማት ተሰጥቷል። የጌታዘሩ ስፖርት ክለብ ተጫዋች ዮዲት አዲሱ የሊጉ ኮከብ ተጫዋች ሆና የተመረጠች ሲሆን የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አሰልጣኝ ገነት ጴጥሮስ ደግሞ ኮከብ አሰልጣኝ ሆና ተመርጣለች። የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የሊጉ ሻምፒዮን በመሆኑ የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን የጌታዘሩ ስፖርት ክለብ የጸባይ ዋንጫ ተሻላሚ ሆኗል። የጌታዘሩ ስፖርት ክለብ ተጫዋች ዮዲት አዲሱና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ተጫዋች ፋኖ ከበደ ከመጪው ዓመት ጀምሮ በሲሸልስ 'ብራስሊን' ለተሰኘ የቮሊቦል ክለብ ለመጫወት መፈራረማቸው በዚሁ ጊዜ ተገልጿል። ወላይታ ድቻ በወንዶች የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የዓመቱ አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል። በሌላ በኩል የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ውድድር ዛሬ በትንሿ ስታዲየም ተጀምሯል። በውድድሩ ላይ በወንዶች ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ደቡብና ትግራይ ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሴቶች ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ውጪ ሌሎቹ ሁለት ክልሎችና ከተማ አስተዳድሮች ይሳተፋሉ። በውድድሩ ላይ ቀሪዎቹ ስድስቱ ክልሎች በበጀት ምክንያት አለመሳተፋቸውን የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን አስታውቋል። ውድድሩ በቮሊቦል ስፖርት ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራትና በሁለቱም ጾታዎች በሚካሄደው የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ብቁ የሆኑ ተጫዋቾችን መመልመል ዋንኛ ዓላማው አድርጓል። በውድድሩ መክፈቻ ቀን በወንዶች አዲስ አበባ በሶስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቤኒሻንጉል ጉምዝን ሶስት ለዜሮ አሸንፏል። ውድድሩ እስከ ሰኔ 23 ቀን 2010 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ትንሿ ስታዲየምና የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ውደድሩ የሚካሄድባቸው ስፍራዎች ናቸው።