የአማራ ክልል ሴቶች ሁሉን አቀፍ የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ሴቶች ሁሉን አቀፍ የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው
ኢዜአ ህዳር 15 / 2012 በኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች ቦታውን በችሎታ እንጂ በችሮታ ያገኙት አለመሆኑን ለማስመስከር ጠንክረው መስራትና ውጤታማ መሆን እንዳለባቸው ተገለጸ። የአማራ ክልል ሴቶች ሁሉን አቀፍ የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው። በውይይቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የፌደራል ትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እንደገለጹት ወቅቱ ሴቶች በአገሪቱ ትልልቅ የሥራ ኃላፊነት ቦታዎች ሳይቀር የሚገኙበት ነው። ለእዚህም ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ ተሰይመው ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን በማሳያነት ገልጸዋል። ቀደም ባሉት ጊዜያት በተሳሳተ አረዳድ ሴቶች ፖለቲካዊ አቅም እንደሌላቸው አድርጎ በማሰብ ሁሉ ነገር ለወንዶች ይተው እንደነበርም አስታውሰዋል። "አሁን ባለው ሥርአት የአተገባበር ችግር ካልሆነ በስተቀር ከህገመንግስቱ ጀምሮ የሚወጡ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች የሴቶችን ሁለተናዊ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ያረጋገጡ ናቸው" ብለዋል። ሴቶች በየደረጃው የተሰጣቸው ኃላፊነት በችሮታ ሳይሆን በችሎታቸው ያገኙት መሆኑን ለማሳየት በርትተው ከመስራት ባለፈ አርአያ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል። "በክልሉ በኃላፊነት ደረጃ ላይ ያሉ ሴቶችም ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ሴት አመራሮች ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ሊረባረቡ ይገባል" ብለዋል። የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አስናቁ ድረስ በበኩላቸው ሴቶች አሁንም ተደራጅተው መብታቸውን በማስጠበቅ በኩል ውስንነት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት። "ህገመንግስቱ የሴቶችን እኩልነት ያረጋገጠ ቢሆንም በየደረጃው ያሉ አስፈፃሚ አካላት የአተገባበር ውስንነት ይስተዋልባቸዋል" ብለዋል። ይህንን ለመከላከልና በየዘርፉ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ሴቶች ህግን መሰረት አደርገው በመደራጀት ሊጠይቁ እንደሚገባ አመልክተዋል። በመድረኩ ላይ "የሴቶች ተሳትፎና የአገር ልማት" በሚል የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ፣ ሴቶች ሲሰጣቸው እንጂ "ይገባኛል" የሚል ጥያቄ በማንሳት በኩል ክፍተት እንዳለባቸው ገልጸዋል። " አሁንም ወንዶችን የበላይ አደርጎ የመሳል ዝንባሌ ከወንዶች ብቻ ሳይሆን ከሴቶችም ጭምር አልፎ አልፎ ሲንጸባረቅ ይስተዋላል" ብለዋል። ዶክተር ሙሉነሽ እንዳሉት ይህንን የተሳሳተ ዝንባሌ ከመሰረቱ ለማስወገድ ሴቶች እራሳቸውን ከወንዶች እኩል እንደሆኑ ማሰብና በተግባር ሆነው መገኘት ይኖርባቸዋል። ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የውይይት መድረክ ከቀበሌ እስከ ክልል ያሉ ሴት አመራሮችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ ሆነዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።