በአጎራባች ክልሎች ያለው ሰላምና መረጋጋት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በአጎራባች ክልሎች ያለው ሰላምና መረጋጋት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ተባለ
ኢዚአ ህዳር 15 /2012 በምስራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎች አሁን ያለው ሰላምና መረጋጋት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ የመከላከያ ሚኒስቴር አስገነዘበ ። የምስራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎች የፀጥታ ምክር ቤት የምክክርና የሠላም መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሔዷል። በዚህ ወቅት በመከላከያ ሚኒስቴር የምስራቅ ዕዝ የዘመቻ አዛዠ ኮሎኔል መንገሻ ፋንታው እንደገለጹት በዚህ ዓመት በምስራቅ ኢትዮጵያ የተከሰተው የሠላም መደፍረስ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል። በተለይ በሐረርና ድሬዳዋ ከተማ፣በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ እንዲሁም በአፋርና ሶማሌ ክልሎች መካከል ተከስተው የነበሩ ግጭቶች በፊት የነበረውን የጸጥታ ሁኔታ በፍጥነት ወደ ኋላ የመመለስ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰዋል። ክስተቱ ለዩኒቨርስቲዎች የመማር ማስተማር ስራ መስተጓጎል ጭምር ችግር ከመፍጠር ባሻገር የዜጎችን የመንቀሳቀስ መብት በመገደብ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት አድርሷል ብለዋል። የፀጥታ ምክርቤቱ ባደረገው የተቀናጀ እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት በቀጠናው አብዛኛው አካባቢ የተረጋጋና ሠላማዊ ሁኔታ እንዳለ አመልክተዋል። ይሁን እንጂ በአዋሳኝ አካባቢዎች ከድንበር ጋር በተያያዘ የጎሳ ግጭቶች እንደሚስተዋሉና በዚህም ቀላል የማይባል የሰው ህይወት የጠፋበትና የዜጎች ንብረት የወደመበት አጋጣሚ መከሰቱን ገልፀዋል ። በአካባቢው ይስተዋል የነበረውን አለመረጋጋትና ግጭቶችን ለማስቆም በተደረገው ጥረትም በሶማሌ፣ አፋርና ኦሮሚያ ክልሎች መካከል የእርስ በርስ ግንኙነት መሻሻል አሳይቷል ። በህገወጥ የጦር መሣሪያና በኮትሮባንድ እንቅስቃሴ ቁጥጥር ላይ ትኩረት ተሰጥቶት ሰፊ ስራ መሰራቱንም ኮሎኔል መንገሻ ጠቁመዋል። በዚህ ረገድ ከተገኘው ውጤት መካከል በህገወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 333 ሽጉጦች፣ ክላሽን ጠብመንጃዎች ፣ ብሬንመትረየስ ፣ የተለያዩ ጥይቶችና የእጅ ቦንቦች የተያዙ ሲሆን በህገወጥ መንገድ ወደ ስደት ሊወጡ የነበሩ ሰዎች ተይዘው ወደመጡበት አካባቢ እንዲመለሱ ተደርጓል ብለዋል። በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የተሳተፉ 11 ሰዎች መያዛቸውም ኮሌኔሉ አያይዘው ገልፀዋል ። በአሁኑ ወቅት በቀጠናው የሚታየውን አንፃራዊ ሰላም ለማጠናከር በቀጣይም ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በቀጠናው የህግ የበላይነትን ለማስከበር፣ወንጀለኞችን ለመያዝና ለቀጣዩ ምርጫ የተደላደለ ሁኔታን መፍጠር ከሁሉም የጸጥታ አካላትና ከህዝቡ የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል። የተጀመሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረኮችን በማጠናከር ህዝቡን የማግባባት፣የማስታረቅና የተበደለውን አካል የመካስ ስራ የምክር ቤቱ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንዳለበትም አመላክተዋል። የኦሮሚያ ክልል የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀነአ ያደታ በበኩላቸው የጥፋት ሃይሎች ሃገሪቱን ለማተራመስ የሚያደርጉት ሙከራ እንዳልተሳካላቸውና ለወደፊቱም እንዳማይሳካላቸው ገልጸዋል። ሰላም ወዳዱን ህዝብና ጠንካራ የጸጥታ ኃይል ይዘን የማንሻገረው ተግዳሮት የለም ሲሉ የቢሮው ኃላፊ ተናግረዋል ። የጸጥታ ምክር ቤቱ ለቀጠናው ሰላም መስፈን አበክሮ በመስራት ላይ እንደሆነ አመልክተው መድረኩ የተዘጋጀውም ባለፉት ሶስት ወራት በምክር ቤቱ የተሰሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት ለቀጣይ ስራችን መነሻ የሚሆን አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነው ብለዋል ። የፌዴራልና የክልል ፀጥታ አካላት በተቀናጀ መልኩ በመስራት የፀጥታ ስጋቶች ከማጋጠማቸው በፊት ሁኔታዎችን በማገናዘብ አስቀድሞ የመከላከል ስራ ላይ በንቃት ሊሰማሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ለአንድ ቀን በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ ከአሮሚያ፣አፋር፣ሶማሌ፣ሐረሪ ክልሎችና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ የፀጥታ አካላት፣የፌዴራል ፖሊስና የሃገር መከላከያ ሠራዊት አባላትና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።