ቀጥታ፡

የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል የመሰረተ ልማት ግንባታ በቅርቡ ይጀመራል

ኢዜአ ህዳር 15/2012 የኦጋዴንን የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል የመሰረተ ልማት ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመር የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ያዘጋጀው ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የማዕድን ማውጣት ኮንፍረንስና ኤግዚቢሽን ዛሬ ተከፍቷል። በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የማዕድን ማውጣት ኮንፍረንስና ኤግዚቢሽን መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ እንደተናገሩት ከሁለት ዓመት በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ በኦጋዴን የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ለገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ነው። ለዚህም በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች ማከናወን አስፈላጊ በመሆኑ በቅርቡ የተፈጥሮ ጋዝ የማውጣት ስራውን ከሚያከናውነው ኩባንያ ጋር ስምምነቶች እየተጠናቀቁ መሆኑንም አክለዋል። ከኦጋዴን እስከ ጅቡቲ የሚደርስ የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ እና ማቀነባበሪያ የቧንቧ መስመር ግንባታ እንደሚከናወንም ገልጸዋል። የተፈጥሮ ጋዝ የማውጣት ስራው ረጅም ጊዜና ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑም ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል። እንደ ዶክተር ሳሙኤል ገለጻ በማዕድን ዘርፉ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታን ለመፍጠርም የማሻሻያ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል። የማዕድንና የነዳጅ ስራዎች ፖሊሲዎች መዘጋጀታቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በቅርቡ ጸድቀው ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል። ፖሊሲዎቹ የስነ ምድር መረጃን ለማዘመን የጥራትና የተደራሽነት ክፍተቶችን በመፍታት ረገድ ለውጥ እንደሚያመጡም ነው የተናገሩት። ፖሊሲው በዘርፉ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎችን ማመላከት፣ የተጨማሪ እሴት ስራዎችን ማከናወን፣ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማሳደግ፣ የስራ እድል ፈጠራን ማሻሻልና ሌሎች ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩትም ጠቅሰዋል። በዘርፉ ያሉ እንቅፋቶችንም ለማስወገድ የሚያስችሉ የህግ ማሻሻያ ስራዎች መከናወናቸውና የማዕድን ዘርፉን መምራት የሚያስችል አደረጃጀት የመፍጠር ስራ መሰራቱንም ሚኒስትሩ አክለዋል። ከማዕድን ማውጣት ስራዎች ጋር በተያያዘ አስተዳደራዊ ጉዳዮችንና ቀልጣፋ መረጃን በኦን ላይን አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል አገር አቀፍ አሰራርም ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል። በአገሪቷ በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች ኩባንያዎች ከደህንነት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታትና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ አገር አቀፍ ኮሚቴ መቋቋሙን ጠቁመዋል። በበጀት አመቱ ሶስት ወራት ውስጥም 5 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ወደ 30 የሚደርሱ በማዕድን ዘርፉ ለመሰማራት ጥያቄ ላቀረቡ ኩባንያዎች ፍቃድ መሰጠቱን ከማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 350 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው በኦጋዴን ካሉብ እና ሒላላ በተባሉ ሁለት ቦታዎች ከስምንት እስከ አስር ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ የሚደርስ የተፈጥሮ ጋዝ እንደሚገኝ ይገመታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም