ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብቷ ለድርድር የሚቀርብ አለመሆኑን ህብረተሰቡ ማወቅ አለበት ... ምክር ቤቱ

ኢዜአ ህዳር 15/2012 ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብቷ ለድርድር የሚቀርብ አለመሆኑን ማስገንዘብ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ምክር ቤት አሳሰበ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ግብፅ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመለከተ የምትሰራው አሉታዊ ዲፕሎማሲ መሰረተ ቢስ መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እያስረዳ መሆኑን ገልጿል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የሩብ ዓመት ዕቅድ ገምሟል። ኢትዮጵያ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጨምሮ በአባይ ተፋሰስ ፕሮጀክቶችን የመገንባትና የማልማት ተፈጥሯዊ መብት አላት። ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ፍትሃዊና ምክንያታዊ በመሆነ መንገድ መጠቀም ሲባል በሌሎች ላይ ጉልህ ጉዳት አለማድረስ መሆኑም ይታወቃል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ እንዳሉት፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግድቡን በተመለከተ ለኅብረተሰቡ በቂ መረጃ እያደረሰ አይደለም። ኢትዮጵያ አባይን በተመለከተ መጠቀም የምትችለው እስከምን ድረስ ነው፤ ግድቡ በተፋሰሱ አገራት የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምንድን ነው የሚለውን በግልጽ ሁሉም እንዲያውቀው አልተደረገም ብለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በግድቡ ዙሪያ ለዲፕሎማቶች የሚሰጠውን ማብራሪያ ያህል ለሁሉም ኅብረተሰብ በቂ ግንዛቤ እየተፈጠረ አይደለም ብለዋል። በመሆኑም ኢትዮጵያ በግድቡና በአባይ ተፋሰስ ላይ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት እንዳላት በኅብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚከታተሉት ፕሮጀክት በመሆኑ ለኅብረተሰቡን በቂ መረጃ እንዲደርስ አሳስበዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ግብጽ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመለከተ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የጀመረችው አሉታዊ ዘመቻ ከእውነት የራቀ መሆኑን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን የምታሳትፍበት ርቀት ብዙ የዓለም አገሮች የማያደርጉትን ነው ብለዋል። ይሁን እንጂ ግብፅ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የኢትዮጵያን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ የሚገነባ ፕሮጀክት እንደሆነ አድርጋ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የምትገልጽበት መንገድ ስህተት እንደሆነ አስረድተዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተግባር ሃይል ማመንጨት ስለሆነ ውሃው ሃይል ካመነጨ በኋላ ይመለሳል፤ ከዚህ በተቃራኒ ስለግድቡ የተሳሳተ መረጃ መስጠት ግን ስህተት ነው ብለዋል። ይህን በተመለከተ "በአዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማኅበረሰቡን ጠርተን ግልጽ ማብራሪያ ሰጥተናል፤ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል" ነው ያሉት። ግብጽ አባይን ለውስጥ ፖለቲካ ልትጠቀምበት ፈልጋ እንጂ ኢትዮጵያ ሃላፊነት በጎደለው መንገድ የተፋሰሱን አገራት የሚጎዳ ፕሮጀክት አትገነባም ብለዋል። ኢትዮጵያ አባይን የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብቷን ለማስከበር የማንንም ድጋፍ እንደማትሻ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ተፈጥሯዊ መብቷን ለመጠቀም ከማንም ጋር ለድርድር አትቀርብም ብለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም