የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ማዕከሉ ኢትዮጵያን በዓለም -አቀፉ ገበያ የአፍሪካ መግቢያ በር ያደርጋታል- ጃክ ማ - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ማዕከሉ ኢትዮጵያን በዓለም -አቀፉ ገበያ የአፍሪካ መግቢያ በር ያደርጋታል- ጃክ ማ
ኢዜአ፤ ህዳር 15/2012 ኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ማዕከል መሆኗ አገሪቱን በዓለም አቀፉ ገበያ የአፍሪካ መግቢያ በር እንደሚያደርጋት ግዙፍ የኦንላይን ግብይት ኩባንያ 'አሊባባ' መስራችና ሊቀመንበር ጃክ ማ ተናገሩ። የኢትዮጵያ መንግስትና እና አሊባባ ኩባንያ በኤሊክትሮኒክስ የታገዘ ዓለም-አቀፍ የንግድ መገናኛ ማዕከል (hub) በኢትዮጵያ ለመገንባት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ የተፈረመው ኩባንያው መስራችና ሊቀመንበር ጃክ ማ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በተገኙበት በአይ.ሲ.ቲ ፓርክ በተከናወነ ስነ-ስርዓት ነው።
ኢትዮጵያና የአሊባባ ኩባንያ በተጨማሪም በዲጂታል ኢኮኖሚ አቅም ግንባታና የተቀናጀ የኤክትሮኒክስ ግብይት ማዕከል በመፍጠር ረገድ በትብበር መስራት የሚያስችላቸውን ሌሎች ስምምነቶችንም ፈርመዋል።
በስምምነቱ መሰረት በኢትዮጵያ የሚገኙ አነስተኛና መካካለኛ ኢንተርፕረይዞች ቻይናን ጨምሮ ድንበር ተሻጋሪ ግብይቶችን ሲፈጽሙ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሎጂስትክ አገልግሎት የሚያገኙ ይሆናል።
የኩባንያው መስራችና ሊቀመንበር ቻክ ማ በስነ-ስርዓቱ ላይ ወጣቶች፣ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችና ታዳጊ አገራት በዓለም አቀፉ ገበያ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መብት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ባለፉት ጊዜያት ልኡላዊነት (ግሎባላይዜሽን) በአውሮፓና አሜሪካ መመራቱን አስታውሰው፤ አሁን ግን እንደኢትዮጵያ ያሉ ጠንካራ አመራር ያላቸው ታደጊ አገራት የመሪነቱን ሚና ሊረከቡ ይገባል ብለዋል።
"ኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት አፍሪካ በዓለም የምትታይበት መስኮት ሆና አገልግላለች" ያሉት ጃክ ማ፤ በመጪው ጊዜም ኢንተርኔትን ጨምሮ አለም ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች የዳበረ ምጣኔ ኃብት (ዲጂታል ኢኮኖሚ) አማካኝነት ኢትዮጵያ የአፍሪካ መግቢያ በር ሆና እንደምትቀጥል አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የሚመዘገበው ስኬት አፍሪካውያን ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚሰጠውን ፋይዳና እድል እንዲጠቀሙ እንደሚያነቃቃ በመጠቆም።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ውይይትም ኢትዮጵያ ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች፣ ወጣቶችና ሴቶችን ለማብቃት ያላትን ቁርጠኝነት መረዳታቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን "ትራንስፎርሜሽን የሚፈልጋቸው አይነት መሪ" ሲሉ ገልጸው፤ አፍሪካ እንደጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አይነት ለወጣቶች የሚጨነቁ መሪ እንደሚያስፈልጓት ተናግረዋል።
አያይዘውም ኩባንያቸው በየዓመቱ ለአፍሪካ ሥራ ፈጣሪዎች ይሰጥ የነበረውን የ10 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በአሁኑ ወቅት ወደ100 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ መወሰኑንም አስታውቀዋል።
በተያዘው ዓመት በስማቸው የመሰረቱት ፋውንዴሽን በጋና 10 ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን አወዳድሮ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ ፋውንዴሽናቸው በቀጣይ ዓመት መሰል እድል በኢትዮጵያ ለመከወን መወሰኑን ይፋ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው "የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ፍትሃዊ የሆነ የንግድ ውድድር ሜዳን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አቅም አለው" ብለዋል።
ይህም ኢትዮጵያ በቀጣይ አስር ዓመታት በአፍሪካ አምስቱ ግዙፍ ምጣኔ ኃብታዊ አቅም ያላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ የያዘችውን እቅድ ለማሳካት ሚናው የጎላ መሆኑን በመግለጽ።
መንግስታቸው የታቀደው የኤሌክትሮኖክስ ግብይት ማዕከል እንዲሳካ የበኩሉን ሁሉ እንደሚያደርግም ጨምረው ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት (eWTp) በአሊባባ ሀሳብ አመንጪነት በአውሮፓዊያን 2016 የተቋቋመ የኢንተርኔት ቀጥታ ግብይት ስርዓት ሲሆን ዓላማውም አነስተኛና መካከለኛ ሥራ ፈጣሪዎች ምርቶቻቸውን ለገበያ በማቅረብ ሂደት የሚያጋጥማቸውን ችግር መፍታትና ምጣኔ ኃብታዊ እድገትን ማፋጠን ነው።
ኢሊባባ በአሁኑ ወቅት በዓመት አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚጠጋ የኦንላይን ግብይት የሚያደርግ ግዙፍ ኩባንያ ሲሆን፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በዓለም ላይ ለ40 ሚሊዮን ሰዎች የስራ እድል ፈጥሯል።