'አጓት' የወተት ኢንዱስትሪውን ተረፈ-ምርት አልባ ዘርፍ ሊያደርገው ነው - ኢዜአ አማርኛ
'አጓት' የወተት ኢንዱስትሪውን ተረፈ-ምርት አልባ ዘርፍ ሊያደርገው ነው
ህዳር 15/2012 ኢትዮጵያ የወተት ኢንዱስትሪ በተረፈ-ምርትነት ሲያስወግደው የኖረውና ከፍተኛ የፕሮቲን ይዘት ያለው 'አጓት' ዘርፉን ተረፈ-ምርት አልባ የሚያደርግበት የጥናት ውጤት ተግባራዊ እየሆነ ነው። "የወተት ተዋጽኦ ከሆኑት እርጎ፣ ቅቤ፣ አሬራና አይብ ቀጥሎ በሚገኘው 'አጓት' ፕሮቲን-አጠር ምግቦችን በፕሮቲን ማበልፀግ ይቻላል" ይላል የጥናቱ ግኝት። ከሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል የተገኘውን ይህን ጥናት ወደ ተግባር ለመቀየርም ከአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ የጁስና ዳቦ ምርት ኢንተርፕራይዝ ሥራ ፈጣሪዎች ተግባር ተኮር ስልጠና ተሰጥቷል። ስልጠናው የአጓትን ከፍተኛ ፕሮቲን በመጠቀም የአቮካዶ፣ የዘይቱን፣ የፓፓያና የማንጎ ጁሶች ከቫይታሚን በተጨማሪ በፕሮቲን እንዲበለፅጉ የሚያስችል ነው ተብሏል። ዳቦ ባለው ከፍተኛ የካርቦሃይድሬት ምግብ ይዘት ላይም ተጨማሪ ፕሮቲን አካቶ ማግኘት የሚያስችል ነው። የጥናቱ ውጤት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲሆን ሥራ ፈጣሪ ኢንተርፕራይዞችን፣ የምርቱን ተጠቃሚዎችና ወተት አምራች ኢንዱስትሪዎችን እንደሚጠቅም የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ መኮንን ጋሹ ለኢዜአ ገልፀዋል። እንደ አቶ መኮንን ገለጻ ተረፈ-ምርት የነበረው 'አጓት' በአካባቢ ሥነ-ምህዳር ላይ ሲያደርስ የቆየውን ተፅዕኖ ለመቀነስም ጭምር ጠቀሜታ ይኖረዋል። ለዚህ ግብዓት የሚሆነው 'አጓት' መገኛው የት ነው? ሲል ኢዜአ ላነሳው ጥያቄ የኢንስቲትዩቱ ወተት ኢንዱስትሪ ግብዓት ቡድን መሪ አቶ አራርሳ ጉተማ 'ከወተት አምራች ኢንዱስትሪዎች ለመጠቀም ቀድሞ ታሳቢ ስለ መደረጉ ምላሽ ሰጥተዋል። 40 ያህል ወተት አምራች ኢንዱስትሪዎች በአገሪቷ መኖራቸውንና ለዚህም ኢንስቲትዩቱ በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ስልጠናውን በመጠቀም ዳቦ ላይ እሴት በመጨመር በይዘትና በዋጋ ተወዳዳሪ ዳቦ ለማቅረብ ማቀዷን የተናገረችው የሽመልስ መስፍንና ጓደኞቹ የዳቦ ኢንተርፕራይዝ አባል ወይዘሮ እመቤት ዘነበ ነች። ወይዘሮዋ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በሳምንት ሁለት ቀን በፕሮቲን የበለፀገ ዳቦ ለአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ምገባ ፕሮግራም ለማቅረብ መዘጋጀቷን ገልፃለች። ይህን የቢዝነስ ሐሳብ ተግባራዊ ስታደርግ ከመጠቀሟ ባሻገር ልጆችም ለዕድገታቸው አስፈላጊ የሆነውን ፕሮቲን እንዲያገኙ እንደሚያስችላቸው እምነቷን ተናግራለች። ወይዘሮ እመቤት ከሥልጠናው በኋላ ወደ ሥራ ለመግባት የአጓት መገኛ ከሆኑት ወተት አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ዋጋና ማጓጓዣ ለማመቻቸት ኢንስቲትዩቱን እያነጋገረች መሆኗን ነው የገለጸችው። ተረፈ ምርት የነበረው አጓት ዳቦና የተለያዩ ጁሶች በነበራቸው የምግብ ይዘት ላይ ተጨማሪ እንዲኖራቸው ከማስቻሉ በላይ ከእንጀራና ሌሎች ምግቦች ጋር ለማዘጋጀት ገደብ እንደሌለውም ጥናቱ አመላክቷል። የወተት ኢንዱስትሪዎችም ሲባክን የነበረውን አጓት ለሸያጭ በማቅረብ የማምረቻ ወጪያቸውን እንዲያካክሱ በማገዝ በዋጋ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ነው የተባለው።