ቀጥታ፡

የብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር በመሆኑ ከጨፍላቂነት ይልቅ አቃፊነቱ የጎላ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

ህዳር 14/2012 የብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር በመሆኑ ከጨፍላቂነት ይልቅ አቃፊነቱ የጎላ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) ሊቀ መንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። የኢህአዴግ ውሕደትና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) 39ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ለአዴፓ ትረጉሙ ከፍ ያለ መሆኑን የገለጹት የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ ደመቀ መኮንን፤  ''በመጣንበት መንገድ ያጎደልናቸውን ሞልተን የተሻለች አገር ለመፍጠር የብልጽግና ፓርቲ መልካም አጋጣሚ ይዞ መጥቷል'' ብለዋል። የአዴፓ 39ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ከፍተኛ የመንግሥትና የፓርቲ ኃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተከብሯል። በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢህአዴግ ሊቀ መንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር በመሆኑ ከአግላይነትና ጨፍላቂነት የተላቀቀ አካታች መሆኑን ተናግረዋል። ምሁራንንና አርብቶ አደርን ያላከተተ ፓርቲ ጨፍላቂ ሳይባል አካታቹ ጨፍላቂ ሊባል የሚቻልበት አመንክዮ አለመኖሩን ነው ዶክተር አብይ ያብራሩት። የሲዳማ ሕዝብ ራሱን ለማስተዳደር እንዲወስን የፈቀደ ፓርቲ ጨፍላቂ ሊሆን እንደማይችል ያመለከቱት ሊቀ መንበሩ፤ አዲሱ ፓርቲ ጨፍላቂ ቢሆን ኖሮ ለሕዝበ ውሳኔ ዕድል ሊሰጥ እንደማይችል አስገንዝበዋል። በዚህ ወቅት በተጨባጭ ችግር ቢያጋጥምም ኢትዮጵያን ሊያፈርስ የሚችል ኃይል ግን ተፈጥሮ እንደማያውቅና ወደፊትም ሊፈጠር እንደማይችል የተናሩት ዶክተር አብይ፤ በፍቅርና ይቅርታ በጋራ ለጋራ አገር ግንባታ መቆም ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዝ አመላክተዋል። የአዴፓ ሊቀ መንበርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ''አሁን የምንፈጥረው ፓርቲ በሦስት ትውልድ ቅብብሎሽ የመጣ ነው፤ ስለዚህ ቀጣዩ ትውልድ ያለፉ መልካም ሥራዎችን እንደወረት ወስዶ አገርን በጋራ ለመለወጥ ይሠራል'' ብለዋል፡፡ ሁልጊዜም ከመልካሙ ነገር እንነሳለን እንጅ አፍርሰን ከባዶ አንገነባም፤ ይህ የትም አያደርሰንም'' ማለታቸውን አብመድ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም