ቀጥታ፡

ክልሉ የመጀመሪያው የማርች ባንድ ባለቤት ሆነ

አሶሳ ኅዳር 14 ቀን 2012 የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጀመሪያው የፖሊስ ማርች ባንድ ባለቤት ሆነ።

ለባንዱ ዛሬ በአሶሳ ከተማ አቀባበል ተደርጎለታል።

በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሙዚቃ ክፍል አስተባባሪና አሰልጣኝ ምክትል ኮማንደር ተስፋዬ ከበደ እንደረተናገሩት ባንዱ በኮልፌ ፖሊስ ልዩ ልዩ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ለ14 ወራት ስልጠና ተከታትሏል።

በዚህም የሙዚቃ ንድፈ ሃሳብ፣ ደረቅ ሶልቬጅ፣ ኖታ ስኬልና ማንበብ ስልጠና መከታተሉን አስታውቀዋል፡፡

ባንዱ 18 ሴቶችን ጨምሮ 91 አባላት ያሉት ሲሆን፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች እንደተሟሉለት ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር መሐመድ ሐመደኒል በዚሁ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ባንዱ የሕዝቦችን ባህልና የአገሪቱን እምቅ ሃብት ማስተዋወቅ ዋነኛ ዓላማው ነው፡፡

ክልሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገኛ መሆኑን ተከትሎ የሚመጡ እንግዶች አጅቦ መቀበልና ማስተናገድ ሌላው ድርሻው እንደሚሆንም አመልክተዋል፡፡

ባንዱ የኪነ-ጥበብ አቅሙን አሟጦ በመጠቀም ኅብረተሰቡን ማነሳሳት እንደሚጠበቅበት ኮሚሽነሩ አሳስበዋል፡፡

መንግሥታዊና ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ባንዱን ለሕዝባዊና ለአገራዊ ጉዳዮች መጠቀም እንደሚችሉ ገልጸው፣ ድጋፍ እንዲያደርጉለት ጠይቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ የማርች ባንድ ስልጠና የሚሰጠው በፌዴራል ፖሊስና በመከላከያ ማርች ቡድኖች መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም