በትግራይ የሚነገሩ ቋንቋዎችን የጥናት ፣ ምርምርና የአካዳሚ ቋንቋዎች ለማድረግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ የሚነገሩ ቋንቋዎችን የጥናት ፣ ምርምርና የአካዳሚ ቋንቋዎች ለማድረግ እየተሰራ ነው
አክሱም ኅዳር 14 ቀን 2012በትግራይ ክልል የሚነገሩ ቋንቋዎችን የጥናት፣ ምርምርና የአካዳሚ ቋንቋዎች ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የትግራይ ቋንቋዎች አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ገለጹ።
ሰባተኛው አገር አቀፍ የትግራይ ቋንቋዎች ሲምፖዚዬም በአክሱም ከተማ ተካሂዷል።
ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ዳንኤል ተክሉ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት አካዳሚው ትግርኛ፣ሳሆና ኩናምኛ ቋንቋዎች የሳይንስና ምርምር እንዲሁም የአካዳሚ ቋንቋዎች እንዲሆኑ በመሥራት ላይ ነው።
አካዳሚው ሕዝቡ በራሱ ቋንቋዎች ተጠቅሞ ሕይወቱን የሚያሻሽልበት ሁኔታ ለማመቻቸትና ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።
መቐለ ዩኒቨርሲቲ የሳሆና የኩናምኛ ቋንቋዎችን ለማስተማር ሥርዓተ ትምህርት ለመቅረጽ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ዶክተር ዳንኤል ተናግረዋል።
በቋንቋዎቹ በስዋስው፣በአጻጻፍና በሥርዓተ ነጥብ አጠቃቀም የሚታዩትን ችግሮች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት እየሰራ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በክልሉ በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ቋንቋዎቹን ለማስተማር እንቅስቃሴ መጀመሩን አመልክተዋል።
የትግራይ ሕዝብ ማንነት፣ ቋንቋና ባህል የሚያስተዋውቁ መጻህፍት እየታተሙ መሆናቸውን ዶክተር ዳንኤል ገልጸዋል።
''በሳሆ ቋንቋ ልማዳዊና ተፈጥሮአዊ የጾታ ስያሜ'' በሚል ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶክተር ንጉሤ ደስታ እንዳሉት ጽሑፉ ኅብረተሰቡ የሚጠቀምባቸውን ተፈጥሮአዊና ልማዳዊ ስያሜዎች ቃላት በመሰነድ አዲስ ትውልድ እንዲጠቀምባቸው ያግዛል።
ቋንቋው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሰጠት እንደሚኖርበት ገልጸው ፣ በተለይ በእድገት ላይ የሚገኙትን ሳሆና ኩናምኛ ቋንቋዎችን ትንሳዔ ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
ቋንቋ የማንነት ፣ ባህል፣ ታሪክና እውቀት ጥላ ነው'' ያሉት ምሁር ፣ ቋንቋዎችን የመግባቢያ ብቻ ሳይሆን የምርምርና ፍልስፍና እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
የኩናማ ብሄር ተወላጁ አቶ አሸብር ፋንታዬ በበኩላቸው ኩናምኛ ቋንቋ እያደገ ቢሆንም በዘፈን፣በሥነ ጽሑፍና በኅትመት ሥራዎች ለማሳደግ የብሄሩ ተወላጅ ምሁራን መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ለኅብረተሰቡ በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ ኅብረተሰቡን የሚጠቅሙ የምርምርና ዕውቀት ጽሑፎች በመተርጎም በቋንቋው ዕውቀቱንና አስተሳሰቡን የሚያሳድግበት ሁኔታ እንዲፈጠር አመልክተዋል።
ምሁራን ቋንቋዎቹ በመገናኛ ብዙኃን፣ በትምህርት ቤቶችንና በምርምር ተቋማት ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ሚናቸውን እንዲጫወቱ ጠይቀዋል።
ሲምፖዚዬሙ ቋንቋዎች እንዲያድጉና በመማር ማስተማር ሂደት ላይ የቋንቋ አጠቃቀምና የአገላለጽ ግድፈቶች እንዲስተካከሉ ያግዛል ያሉት ደግሞ የአክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትግርኛ ቋንቋ መምህርት አስካለ ታደሰ ናቸው።
በሥነ ጽሑፍ፣ በሥነ ልሳንና ባህላዊ ጨዋታዎችና በመማር ማስተማር ሂደት የተዘጋጁትን ሰነዶች ለትምህርት ቤቶች መድረስ አለባቸው ብለዋል።
ለሦስት ቀናት በተካሄደው ሲምፖዝየም ምሁራን፣የቋንቋ ተማራማሪዎችና መምህራን የተሳተፉ ሲሆን ፣ 24 ጥናታዊ ጽሑፎች መቅረባቸው ታውቋል።
ባለፉት ዓመታት በተካሄዱት ሲምፖዚዬሞች የቀረቡት በሥነ ጽሑፍ ፣በሥነ ልሳን፣ በሥነ ቃል ፣ በቋንቋ አጠቃቀም ፣በመዛግብተ ቃላትና ባህላዊ ይዘት ያላቸው ላይ ያተኮሩት 129 ጥናታዊ ጽሑፎች ታትመው ለተጠቃሚዎች መሰራጨታቸው ተገልጿል።