ቀጥታ፡

ፓርኩ ትውልዱ ከመጥፎ የአገሪቱ ታሪክ የሚማርበትና ጠንካሮቹን የሚያጎለብትበትን ተሞክሮ ይዟል

ኢዜአ፤ ህዳር14/2012 ዜጎች ከመጥፎ የአገሪቱ ታሪክ የሚማሩበትንና ጠንካሮቹን የሚያጎለብቱበትን ተመክሮ የሚያንፀባርቀው የአንድነት ፓርክ በተለይ ለወጣቱ ትውልድ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው በደርግ ስርዓት የተገደሉት የ60ዎቹ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከፍተኛ ባለስልጣናት ቤተሰቦች ተናገሩ። በታላቁ ቤተ-መንግስት ቅጥር ግቢ በአዲስ መልክ ታንጾ የተከፈተው የአንድነት ፓርክ ሙዚየም ከያዛቸው ታሪኮች መካከል ደርግ ለእስር ቤትነት ይጠቀምበት የነበረው ጥንታዊ ህንፃ ይገኝበታል። ከላይ የንጉሡ ዙፋን አዳራሽ የሚገኝበት ይህ ህንጻ በንጉሡ ዘመን የወይን ጠጅ ማቆያና የተለያዩ እቃዎች ማስቀመጫ እንደነበር ይነገራል። ወታደራዊው ደርግ ንጉሡን ከሥልጣናቸው በማንሳት አገሪቷን የመምራት ስልጣን ሲይዝ የህንፃውን ላይ መሰብሰቢያው፤ ምድሩን ደግሞ እስር ቤት አደረገው። ደርግ በሥልጣን ዘመኑ የመጀመሪያ ዓመታት ከፈፀማቸው አሳዛኝ ተግባራት መካከል ልክ የዛሬ 45 ዓመት ማለትም ሕዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም የፈፀመው የጅምላ ግድያ ይጠቀሳል። "በደም የታጠበው ቅዳሜ" ተብሎ በሚጠራው በዚህ ዕለት በተለምዶ '60ዎቹ' በመባል የሚታወቁት ከፍተኛ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ባለስልጣናት ግድያ ተፈፅሟል። አብዛኛዎቹ ሟቾች በዚህ የደርግ እስር ቤት ውስጥ ታስረው የነበሩ ሲሆን የወቅቱን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና ሚኒስትሮች ይገኙበታል። የሥርዓቱን አካሄድ ለመቀበል የተቸገሩ ጥቂት የደርግ አባላትም በዚህ ዕለት ከተገደሉት መካከል እንደሚገኙበት የአንድነት ፓርክ ሙዚየም አስተባባሪ አቶ ምንተስኖት ጢቆ ገልጸዋል። ኢትዮጵያዊያኑ የተገደሉበት 45ኛ ዓመት መታሰቢያ በአዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ-ክርስቲያን የፀሎት ስርዓት ተከናውኗል። የሰለባዎቹ ቤተሰቦች በቤተክርስቲያኑ በሚገኘው የሟቾች መካነ ቀብር ላይ የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል። ከፀሎት ሥነ-ስርዓቱ በኋላም የሟች ቤተሰቦች በታላቁ ቤተ-መንግስት ቅጥር ግቢ የአንድነት ፓርክ ሙዚየም የሚገኘውን የደርግ እስር ቤት ጎብኝተዋል። በእስር ቤቱ ያለ ፍርድ በግፍ የተገደሉትን የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ባለስልጣናት ጨምሮ ሌሎች እስረኞች ፎቶግራፎች ይታያሉ። ደርግ ወደ ስልጣን የመጣበትን ሂደትና ሌሎች ተያያዥ የታሪክ ክስተቶች በድምጽ፣ በምስልና በፅሁፍ የሚያስረዱ መረጃዎችንም ይዟል እስር ቤቱ። ኢዜአ በጉብኝቱ ወቅት ያነጋገራቸው 'የ60ዎቹ' ቤተሰቦች እንደገለጹት የተፈጸመው ተግባር እጅግ መሪር ነው፤ ሆኖም ድርጊቱ ታሪክ ሆኖ በሙዚየሙ ለህዝብ መታየቱ መጪው ትውልድ እንዲማርበትና ከዚህ ዓይነቱ ተግባር እንዲቆጠብ ያደርጋል። የዛሬ 45 ዓመት አባታቸው የተገደሉባቸው አቶ አምዴአካለወርቅ እና በወቅቱ የ24 ዓመት ወጣት የነበረውን ወንድማቸውን በሞት የተነጠዉት ወይዘሮ ሀና ታከለ በበኩላቸው ሙዚየሙ መላው ዜጋ ዳግም እንዳይሳሳት ለማስተማር ያግዛል ብለዋል። የአንድነት ፓርክ ሙዚየም አስተባባሪ አቶ ምንተስኖት ጢቆ በአንድነት ፓርክ ውስጥ ለእይታ የቀረቡት መልካምና በጎ የአገሪቱ ታሪክን የሚያንፀባርቁት ሁነቶች አገር ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያዙ ናቸው። ካለፈው በመማር ብሩህ የሆነ ወደፊትን መቃኘት ከዓላማዎቹ መካከል ዋነኛው መሆኑን በመጥቀስ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም