ቀጥታ፡

የግል ባንኮችን የሚያሳትፍ የካፒታል ገበያ ሊጀመር ነው - ብሔራዊ ባንክ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 14 ቀን 2012 በኢትዮጵያ የግል ባንኮችን የሚያሳትፍ የካፒታል ገበያ ለመጀመር ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

የአዋሽ ባንክና ኢንሹራንስ 25ኛ ዓመት ምስረታ በዓል ማጠቃለያ ትናንት ምሽት በሸራተን ሆቴል ተካሂዷል።

ባንኩ የኢዮቤልዩ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የደም ልገሳ፣ የአውደ ርዕይና የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮችን አከናውኗል።

የዛሬ 25 ዓመት ሲመሰረት 24 ነጥብ 2 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል የነበረው ባንኩ አሁን ካፒታሉ 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ደርሷል።

ከ10 ሺህ በላይ ሠራተኞችን ቀጥሮ እያሰራ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ብቻ 890 ሚሊዮን ብር ታክስ መክፈሉን ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ እንደገለጹት በአገሪቷ የሚገኙ የግል ባንኮች ኢኮኖሚውን እንዲደግፉ የአሰራር ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው።

"የባንኮችና ኢንሹራንሶች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም ዘመናዊነት መላበስ ላይ ወደኋላ ቀርተናል" ያሉት ዶክተር ይናገር በቅርቡ የፋይናንስ ዘርፉ ለዳያስፖራ ክፍት መደረጉን አንስተዋል።

የፋይናንስ ዘርፉ ለድህነት ቅነሳ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ዜጎች ተንቀሳቃሽ ንብረታቸውን በዋስትና በማስያዝ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድም መንግሥት ያለሰለሰ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።

ከተንቀሳቃሽ ንብረት ዋስትና ጋር በተያያዘ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ኢንሹራንስ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ የማይክሮ ኢንሹራንስ አገልግሎት በገጠር እንዲስፋፋ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

የፋይናንስ ዘርፉ ተወዳዳሪ፣ ብቁና ዘመናዊ እንዲሆን የሚያስችሉ ስራዎች በአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትኩረት እንደተሰጣቸው የገለጹት የብሔራዊ ባንክ ገዥው የግል ባንኮችን የሚያሳትፍ የመጀመሪያ ደረጃ የካፒታል ገበያ ለማስጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር ይናገር ገለጻ የፋይናንስ ዘርፉን ማዘመንና የሰው ኃይል ማፍራት ላይ የሚሰራ የኢትዮጵያ የፋይናንስ አካዳሚ ለማቋቋምም ዝግጅት ተጀምሯል።

የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጸሀይ ሽፈራው በበኩላቸው ባንኩ የአገሪቷን ኢኮኖሚ በመደገፍ ረገድ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው ለአብነትም 50 ቢሊዮን ብር ብድር በመስጠት ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ ማድረጉን አብራርተዋል።

"መንግሥት የግሉን ዘርፍ ለማበረታታት የጀመራቸው የማሻሻያ እርምጃዎች የሚደነቁ ናቸው" ያሉት ሥራ አስፈጻሚው በተለይም የግል ባንኮችን ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ማበርከት ያስችላቸዋል ብለዋል።

በተለይ መንግስት በባንኮች ላይ ጥሎት የነበረውን የ27 በመቶ ቦንድ ግዥ ማንሳቱ ትልቅ እርምጃ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጸሀይ በቦንዱ ምክንያት የሚያዘው ብር ለብድር ፈላጊዎች የሚውል በመሆኑ ለኢኮኖሚው ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ሲሉ አብራርተዋል።

በቀጣይም ለግል ባንኮች 30 በመቶ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት በመንግስት ይታያል የሚል እምነት እንዳላቸው አክለዋል።

አዋሽ ባንክና ኢንሹራንስ ትናንት ምሽት ለተለያዩ በጎ አድራጎት ማኀበራትና ድርጅቶች ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር 5 ሚሊዮን፣ የኦሮሚያ ልማት ማህበር 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን፣ የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን መርጃ ማዕከል 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ከተበረከተላቸው መካከል ናቸው።

አዋሽ ባንክና ኢንሹራንስ ለደረሰበት ደረጃ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማትም እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም