ቀጥታ፡

የኢህአዴግና የአጋር ድርጅቶች ውህደት የዜጎችን እኩል የመወሰን መብት የሚያረጋግጥ ነው...አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

ጋምቤላ ኢዜአ፤ ህዳር 14/2012 የኢህአዴግና የአጋር ድርጅቶች ውህደት ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ እኩል የመወሰን መብታቸውን የሚያረጋግጥ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ነው ሲሉ የጋህአዴን ሊቀመንበር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።

የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህአዴን) አስቸኳይ ድርጅታዊ ጉባኤ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ጉባኤውን ሲከፍቱ እንደተናገሩት ውህደቱ ጋምቤላን ጨምሮ አምስቱ አጋር ድርጅቶች በአገራቸው ጉዳይ ላይ እኩል የመወሰንና የመጠቀም መብታቸውን የሚያረጋጥ የለውጥ ምዕራፍ ነው።

አምስቱ የኢህአዴግ አጋር ድርጀቶች እስከዛሬ አካታችነትና አቃፊነት በጉደለው መዋቅር በአገራቸው ጉዳዮች የመወሰን መብት ተነፍገው ከመቆየታቸው ባለፈ ያልወሰኗቸውን ጉዳዮች እንዲፈጽሙ ሲገደዱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት አጋር ድርጅቶች የዳር ተመልካችነታቸው ቀርቶ ከኢህአዴግ ጋር በመዋህድ እኩል የመወሰንና የመጠቀም መብታቸውን የሚያረጋገጥ እድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

አቶ ኡሞድ ውህደቱ የአጋር ድርጅቶችን የውሳኔ ስጭነት ሚና ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ እኩል ተጠቃሚነታቸውን ጭምር ያረጋግጣል።

"ውህደቱ ከላይ ከተጠቀሱት መልካም እድሎች ባለፈ አገራዊ አንድነትንና አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ጭምር የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል" ብለዋል።

በአዲሱ የለውጥ ጉዞ ጋህአዴን ከኢህአዴግ ጋር ተዋህዶ የ''ብልጽግና ፓርቲ'' አካል መሆኑ ሁሉንም ተጠቃሚ ስለሚያደርግ ለስኬታማነቱ በትጋት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የዛሬው የድርጅቱ አስቸኩዋይ ጉባኤ ዓላማም የክልሉ መሪ ድርጅት ጋህአዴን ህብር ብሔራዊና አካታች ከሆነው የብልጽግና ፓርቲ አባል የመሆን የመጨረሻ የውሳኔ ሀሳብ ለማሳለፍ መሆኑን አቶ ኡሞድ አስታቀዋል።

በመሆኑን የጉባኤው ተሳታፊዎች በንቃት በመሳተፍ የውህደቱን የመጨረሻ ውሳኔ እንዲያሳለፉ አስገንዝበዋል።

ጉባኤው በአንድ ቀን ቆይታው የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች በሚያደርጉት ውህድት ዙሪያ በስፋት በመወያየት ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

በጉባኤው ላይ ከ600 በላይ የጋህአዴን አመራሮችና አባላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም