በተሽከርካሪ አደጋ የአራት ሰዎች ሕይወት አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
በተሽከርካሪ አደጋ የአራት ሰዎች ሕይወት አለፈ
አዳማ (ኢዜአ) ህዳር 14 ቀን 2012 ዓ.ም---በምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ገለጸ። የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው አለሙ ዛሬ ለኢዜአ እንዳሉት አደጋው ትናንት ከምሽቱ 12፡20 ላይ የደረሰው በዱግዳ ወረዳ ገርቢ ቆርኬ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነው። ከባቱ ወደመቂ ከተማ ሲጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ (ኮድ 3-81008 አ.አ) የሆነ አይሱዚ የጭነት መኪና ከመቂ ወደባቱ ይጓዝ ከነበረ (ኮድ 1-61506 ኦ.ሮ) ባጃጅ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ አደጋው መከሰቱን ግልጸዋል። በአደጋው የባጃጁ አሽከርካሪን ጨምሮ በውስጡ የነበሩ አራት ሰዎች ሕይወታቸው ወዲያውኑ ሲያልፍ ሌሎች ሦስት የባጃጁ ተሳፋሪዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል። ኮማንደር አስቻለው እንዳሉት በአደጋው ሕይወታቸው ካለፈው ሰዎች ውስጥ ሁለቱ ሴቶች ናቸው። ከባድ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሦስቱ ግለሰቦችም በባቱ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን አመልክተዋል። ባጃጁ ከአቅም በላይ ሰባት ሰዎችን አሳፍሮ መጓዙ እና የጭነት መኪናው ከፍጥነት በላይ በማሽከርከር በተፈጠረ የጥንቃቄ ጉድለት አደጋው ሊከሰት መቻሉን ኮማንደር አስቻለው አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅት ያልተጠበቀ ዝናብ እየጣለ በመሆኑ አሽከርካሪዎች የመኪና ፍሬንና የዝናብ መጥረጊያ በአግባቡ መስራቱን ከማረጋገጥ ባለፈ በጥንቃቄ መጓዝ እንዳለባቸው ኮማንደር አስቻለው አስገንዝበዋል።