በአማራ ክልል ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች ፈቃድ ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች ፈቃድ ተሰጠ
ኢዜአ ህዳር 13/2012 ዓ/ም በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ከ19 ቢሊዮን ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን በአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ። ከወቅታዊ ሁኔታው ጋር ተያይዞ በክልሉ ተቀዛቅዞ የነበረው የኢንቨስትመንት ፍሰትም አሁን ላይ እየተነቃቃ መጥቷል። በቢሮው የፕሮሞሽንና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይኸነው ዓለም ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የሆኑ የልማት ዘርፎች ተለይተው ለባለሃብቶች ክፍት ሆነዋል። በዚህም መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ወደ ክልሉ የሚመጡ ባለሃብቶችና ኩባንያዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። በመጀመሪያው ሩብ የበጀት ዓመት ፈቃድ የተሰጠው በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ጨርቃጨርቅ፣ ኬሚካል ማምረት፣ እንጨትና ብረታብረት፣ ግብርና፣ ቱሪዝምና በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማረት ጥያቄ ላቀረቡ ባለሃብቶች ነው። በዚህም ቢሮው ለ554 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ካቀደው በላይ ማከናወኑን ዳይሬክተሩ አመኘልክተዋል። ፈቃዱ የተሰጠው ለ608 ባለሃብቶች ነው። ፈቃዱን ከወሰዱት መካከልም 124 በአግሮ ፕሮሰሲንግ ሲሆን ይህም የአርሶ አደሩን ምርት በግብዓትነት በመጠቀም የገበያ ችግርን ለመፍታት እንሚያግዝ አቶ ይኸነው አስረድተዋል። በተለይ ከ2009 በጀት ዓመት ጀምሮ እንደሀገር ተፈጥሮ ከነበረው ወቅታዊ ችግር ጋር ተያይዞ የክልሉ የኢንቨስትመንት ፍሰት ተቀዛቅዞ እንደነበር አስታውሰዋል። ዘንድሮ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ሊጨምር የቻለው በሁሉም የክልሉ አካባቢ የአገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽ ለማድረግ እስከ ወረዳ ድረስ አደረጃጀት በመዘርጋትና በሰው ኃይል ማሟላት በመቻሉ ነው። ለውጡ ተከትሎም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጅ ዲያስፖራዎችና የውጭ ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም ቢሮው በአዲስ አበባ የኢንቨስትመንት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በመክፈት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች የተሟላ መረጃ መስጠት መቻሉ ለውጤታማነቱ አስተዋጽኦ አድርጓል። ፈቃድ ለወሰዱ ባለሃብቶችም ቢሮው በመነሻ የሊዝ ዋጋ መሬት ለመስጠትና እየተገነቡ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ እንደሚደረግም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ፕሮጀክቶች ግንባታቸውን ጨርሰው ወደማምረት ስራ ሲሸጋገሩ ከ60 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፍጥሩ ይጠበቃል። አቶ አማረ መላኩ የተባሉ ባለሃብት በበኩላቸው በ60 ሚሊዮን ብር ካፒታል ጊዮን የአልሙኒየም ማምረቻ በባህርዳር ለመገንባት በበጀት ዓመቱ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል። ቢሮው የመስሪያ ቦታ ፈጥኖ ከሰጣቸውም በአጭር ጊዜ ገንብተው ወደማምረት ስራ በመግባት ራሳቸውንና ክልሉን ለመጥቀም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። የማምረቻው ግንባታ ሲጠናቀቅም 200 ለሚደርሱ ሰራተኞች የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል እንደሆነም ጠቁመዋል። ባለፈው የበጀት አማት በክልሉ ከ38 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ከአንድ ሺህ 600 የሚበልጡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውም ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።