የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖት አባቶች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እየተወያዩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖት አባቶች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እየተወያዩ ነው
ኢዜአ ህዳር 13/2012 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን እና የእስልምና ሃይማኖት አባቶች በአገሪቱ ወቅታዊ ችግሮች ላይ ውይይት እያደረጉ ነው። ውይይቱ በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አዳራሽ እየተካሔደ ሲሆን ስለ አገርና ሕዝቦች ሰላምና አንድነት ላይ የሚመክር ይሆናል ነው የተባለው። የሐይማኖት አባቶቹ በተለይ በአሁኑ ወቅት ሐይማኖት፣ ፖለቲካና ልዩ ልዩ ችግሮችን ምክንያት በማድረግ ያለአግባብ የሚጠፋው የሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ባተኮሩ ሃሳቦች እንደሚወያዩም ነው የተገለፀው። በአገሪቱ የተከሰቱ ችግሮች መንስኤና መፍትሔዎቻቸው ላይ ውይይት በማድረግ አጥፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ የሚያደርግ ነው ብለዋል። በመጨረሻም ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ምንም አይነት ችግሮች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ ሊሰሩ በሚችሉ ተግባራት ላይ ተወያይተው የጋራ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጡ ተናግረዋል።