ቀጥታ፡

የምርት ደረጃዎች ላይ የሚታይ የግንዛቤ ማነስ ተወዳዳሪነት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል

ኢዜአ ህዳር 13/2012 የኢንዱስትሪ ምርቶች ደረጃ ላይ የሚታይ የግንዛቤ ማነስ ምርቶቹ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆነው እንዳይቆዩ ተጽዕኖ ማሳደሩ ተገለጸ። ተወዳዳሪነትን ያለጥራት በዋጋና አቅርቦት ለማምጣት መፈለግም እንዲሁ ሌላው ችግር ነው ተብሏል። ለክልል ማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አመራሮች የአምራች ኢንዱስትሪዎች የምርት ጥራት ደረጃን በማሻሻል ብቃትና ተወዳዳሪነታቸውን የሚያግዝ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ስልጠናው አምራች ኢንዱስትሪዎች በጥራት በማምረት የምርት ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ፣ ዘርፉን ለሚከታተሉ አመራሮችንም የምርት ደረጃ አስፈላጊነትን ተረድተው ድጋፍ እንዲሰጡ የሚያስችል ነው ተብሏል። የምርት ደረጃ የወቅቱን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ደረጃ ዕድገት መሠረት በማድረግ ምርቱ ለታለመለት ተስማሚ መሆኑን ለማረጋገጥ የራሱን መመሪያ፣ መስፈርትና የፍተሻ ዘዴዎች ይከተላል። ምርቶች ተወዳዳሪና በዓለም ዓቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከማምረት ሂደት ጀምሮ የግብዓት ጥራት መጠበቅ ሲቻል መሆኑን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የደረጃ ትግበራ ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ተፈራ ተናግረዋል። የግብዓት ጥራት ማነስ በምርት ደረጃ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በመቀነስ የምርቱ ተወዳዳሪነትን ለማስፋት የጥሬ ዕቃ ጥራት ወሳኝ ነው እንደሆነም ነው የገለጹት። ችግሩ በምርት ማጓጓዝና ማከማቸት ወቅት የሚፈጠር ሲሆን በአብዛኛው በግብርና ማቀነባበሪያ ምርቶች እንደሚስተዋልና 50 በመቶ ግብዓቶችን ለብክነት እንደሚጋለጡ አስታውቀዋል። የማምረቻ አንዱስትሪዎች በዚህ መንገድ የተገኙ ግብዓቶችን ስለሚጠቀሙ ዝቅተኛ የምርት ደረጃ ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት አቶ መንግስቱ ። የደቡብ ክልል የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አሸቦ ሉሶ ለኢዜአ እንዳሉት አምራቾች ባለማወቅ የችግሩ ሰለባ እንዳይሆኑ ኤጀንሲው ለምርት ብቻ ሳይሆን የግብዓቶችን ደረጃንም ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡ ኢንዱስትሪዎች የሚጠቀሟቸውን ግብዓቶች በመፈተሽና በመመርመር ምርቶቻቸው ተወዳዳሪነታቸው እንዲጨምር “በኢትዮጵያ የተሰራ” የሚል አገራዊ ገጽታን ለዓለም የማስተዋወቅ ድርሻቸውን ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ስልጠናው አምራቾች በጥራት በማምረት ተወዳዳሪነትና በአገር ምርት እንዲኮሩ የሚያስችል ግንዛቤ እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑንም አቶ አሸቦ ጠቁመዋል ። ተጠቃሚዎች አምራቾችን ለማበረታታትና ለከፈሉት ዋጋ ጥራት ባለው ምርት እንዲረኩ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ያረጋገጠውን ደረጃ ልዩ መለያ በማየት መግዛት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ አብዛኛዎቹ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን በዋጋና በአቅርቦት ብቻ ተወዳዳሪ ለመሆን ያላቸው ፍላጎት የዓለምን ገበያ ሰብረው እንዳይገቡ ተጽዕኖ ፈጥሯል ተብሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም