ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ማጠናከር አላማ ያደረጉ ፎረሞች በያዝነው ወር በአዲስ አበባ ይካሄዳሉ

ኢዜአ ህዳር 12/2012  ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ማጠናከር አላማ ያደረጉ ፎረሞች በያዝነው ወር በአዲስ አበባ እንደሚካሄዱ ተገለጸ። በኩዌት የኢትዮ-ኩዌት የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም እየተካሄደ እንደሆነና ዛሬ የደቡብ ኮሪያ ባለሀብቶች በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ የንግድ ማህበረሰብ አካላት ጋር እያደረጉ መሆኑም ተገልጿል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለመገናኛ ብዙሃን ዛሬ ሳምንታዊ መግለጫውን ሰጥቷል። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ከኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አንጻር በያዝነው ወር የንግድና የኢንቨስትመንት ፎረሞች እንደሚካሄዱ ተናግረዋል። በደቡብ ኮሪያ ጨርቃ ጨርቅ ማህበርና ሴኡል በሚገኛው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ትበብር የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ህዳር 19 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ገልጸዋል። ህዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም 12 የሳዑዲ ዓረቢያ ኩባንያዎችን ያሳተፈ የኢትዮ-ሳዑዲ አረቢያ የቢዝነስ ፎረም እንደሚካሄድ ጠቁመዋል። የደቡብ ኮሪያ ባለሀብቶች ያየዘ ሌላ ልዑካን ቡድን በያዝነው ሳምንት አዲስ አበባ መግባቱንና ዛሬ ማምሻውንም ከኢትዮጵያ የቢዝነስ ማህበረሰብ ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል። ባለፈው ሳምንት በደቡብ ኮሪያ ርዕሰ መዲና ሴኡል 38 የደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች የተሳተፉበት የኢትዮ-ኮሪያ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም መካሄዱን አስታውሰዋል። በኩዌት የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላና የኩዌት የንግድ ምክር ቤት በጋራ ያዘጋጁት የኢትዮ-ኩዌት ቢዝነስ ፎረም እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል። እየተካሄዱ የሚገኙትና በቀጣይ የሚካሄዱት የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረሞች ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች ጋር በዘርፉ ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እየሰራች ያለችውን ስራ የሚያመላክት መሆኑን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል። ከዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ጋር በተያያዘ በሳዑዲ አረቢያ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸውን ኢትዮጵያውያን ዜጎች ጉዳይ መንግስት የቅርብ ክትትል እያደረገበት እንደሆነም ነው አቶ ነቢያት በመግለጫው ወቅት የገለጹት። በታንዛንያ፣ የመንና ሱዳን በእስር ቤቶች የሚገኙና በስደት የሚኖሩ ዜጎችም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ስራ እየተከናወነ እንደሆነ ጠቁመዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም