በትግራይ የታዳጊ ወጣቶች አትሌቲክስ ውድድር አጽቢ ወንበርታ ወረደ መሪነቱን ይዟል

80
መቐለ (ኢዜአ) ህዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም--- በትግራይ ክልል ላለፉት ስድስት ቀናት ሲካሄድ በቆየው ከ17 ዓመት በታች ዕድሜ ክልል የታዳጊ ወጣቶች አትሌቲክስ ውድድር አጽቢ ወንበርታ ወረደ መሪነቱን ያዘ። የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ የህዝብ ግንኝነት ባለሙያ አቶ ንጉሰ ኃይሉ ለኢዜአ እንዳሉት ከህዳር ሰባት ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ በተካሄደው ውድድር ፍጻሜያቸውን ያገኙ ውድድሮች አሉ። ለእዚህም በ100 ፣ በ200 እና በ1ሺህ 500 ሜትር የሩጫ እንዲሁም የአሎሎ ውርወራ ውድድሮች ፍጻሜ ማግኘታቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል። በዚህ መሰረት በሴት ተወዳዳሪዎች  አጽቢ ወንበርታ፣ሽረ እንዳስላሴ ከተማና እና ሳምረ ሰሀርቲ ወረዳ በቅደም ተከተል ከአንደኛ እስከ ሦስትኛ ደረጃ ይዘው ውድድሩን አጠናቅቀዋል። በወንዶች ደግሞ ሽረ እንዳስላሴ ከተማ፣ እንዳመኮኒ ወረዳና መቐለ በቀደምተከተል ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ አግኝተዋል። በሴት 200 ሜትር በተካሄደው የሩጫ ውድድር ታዳጊ ሊድያ መብራህቱ ከመቐለ፣ ታዳጊ ማክዳ ፀጋይ እና ፍዮሪ ማርቆስ ሁለቱም ከሽረ እንዳስላሴ በቅደም ተከተል ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ይዘው ወጥተዋል። በወንዶች 200 ሜትር ውድድር ደግሞ ታዳጊ ናትናኤል አሸናፊ ከመቐለ፤ ታዳጊ ሃፍታሙ ታመነ ከእንዳመኾኒ ወረዳ፤ ታዳጊ ዮሴፍ ግደይ ከኦክፍላ ወረዳ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ በቅደም ተከተል ውድድሩን ጨርሰዋል። በዓድዋ ከተማ እየተካሄደ ያለው የታዳጊ ወጣት ዓመታዊ የሻምፒዮና የአትሌቲክስ ውድድር ከነገ በስቲያ ህዳር 14 ቀን 2012 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። በውድድሩ 11 ከተሞችና ወረዳዎች እንዲሁም 8 በፕሮጀክት የታቀፉ ታዳጊዎች ጨምሮ ከ150 በላይ ታዳጊ ስፖርተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም