13ቱ ተጠርጣሪ ግለሰቦች ላይ ዛሬ ክስ ተመሰረተባቸው

64
ህዳር 12/2012 ከሰኔ 15ቱ ግድያ ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት ተብለው በተጠረጠሩ 13 ግለሰቦች ላይ ዛሬ ክስ ተመሰረተባቸው በባህርዳርና አዲስ አበባ ከአማራ ክልል አመራሮችና ከእነ ጀነራል ሰዓረ መኮንን ግድያ ጋር በተያያዘ በወንጀል ድርጊቱ “እጃቸው አለበት” በሚል የተጠረጠሩ 13 ግለሰቦች ዛሬ ክስ ተመሰርቶባቸዋል። የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ለኢዜአ እንደገለጹት ክሱ ከተመሰረተባቸው ተጠርጣሪ ግለሰቦች መካከል የጄነራል ሰዓረ ጥበቃ የነበረው አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡን  ጨምሮ 13ቱም ተከሳሾች ዛሬ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሳቸው ተነቦላቸዋል። በችሎቱም ተጠርጣሪ ተከሳሽ አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ በደረሰበት ጉዳት የተነሳ ችሎቱ የሚጠይቀውን ምላሽ መስጠት  አለመቻሉ ተስተውሏል። በዚህም ችሎቱ “መናገር ካልቻልክ ሀሳብህን በፅሁፍ ግለፅ” ቢለውም ተከሳሹ ይህንንም አለመቻሉ ተመልክቷል። ዛሬ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ከተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች መካከል የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ይገኙበታል። እንደ አቶ ዝናቡ ገለጻ ዓቃቤ ህግም በተከሳሾቹ ላይ " ህገ መንግስትን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል" በሚል ነው ክሱን የመሰረተባቸው። ተከሳሾቹ “በማረፊያ ቤት የደህንነት ስጋት አለብን” በሚልም ለችሎቱ ያቀረቡ ሲሆን፣ በመምርመራ ጊዜም የተወሰዱባቸው ንብረቶች እንዲመለሱላቸውም ጠይቀዋል። ተከሳሾቹ ለቀረበባቸው ክስ የመቃወሚያ ምላሻቸውን ለታህሳስ 1 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲያቀርቡ ችሎቱ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፣ ከደህንነት ጋር ላነሱት ጉዳይ በማረሚያ ቤት ሆነው ጥብቅ ጥበቃ እንዲደረግላቸውም ችሎቱ አዟል። ለምርመራ በሚል ስለተወሰዱባቸው ንብረትም በዝርዝር ለችሎቱ እንዲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ አዟል። ከሰኔ 15ቱ ወንጀል ጋር በተያያዘ ባህርዳር ላይ የአማራ ክልል አመራሮችን ማለትም ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ አቶ ምግባሩ ከበደና አቶ እዘዝ ዋሴ ሲገደሉ እንዲሁም አዲስ አበባ ላይ ደግሞ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት እታ ማጆር ሹም የነበሩት ጄነራል ሰዓረ መኮንን እንዲሁም ሜጀር ጄነራል ገዛኢ አበራ መገደላቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም