ሙዳ፣ ሙራና ሙሪ

29
ገብረህይወት ካህሳይ /ኢዜአ/ ሙዳ ፣ ሙራና ሙሪ  የጃፓን ቃላቶች ናቸው። ለአገራችንም ቢሆን ባእድ አይደሉም። በኦሮሚኛ ቋንቋ ተዘውትረው ይነገራሉ። ሙዳ (muda) በጃፓንኛ ብክነት ማለት ነው። በኦሮሚኛ ደግሞ ሰዎች ይጠቅመኛል ብለው የሚያመልኩበትን ሒደት አመላካች ነው። ሙራ (mura) ከጃፓንኛ የተወሰደ ቃል ሲሆን ትርጉሙም በሰውም ሆነ በማሽን ላይ ያልተመጣጠነ የስራ ክፍፍል ማድረግ ነው። በኦሮምኛ ቋንቋ ደግሞ መቁረጥ አሊያም መወሰን የሚለውን ፍቺ ይይዛል። ሙሪ (muri) እንደ ሙዳና ሙራ ሁሉ የጃፓን ቃል ነው። ሙሪ ሰውን ጨምሮ እንስሳትም ሆኑ ማሽኖች ከአቅም በላይ በማሰራትና በማስጨነቅ ጫና የሚያደርስ አሰራር ነው። ሙሪ የኦሮሚኛ ፍቺው “ቁረጥ” የሚለውን ይተካል። ሶስቱ የጃፓን ቃላቶች ከኦሮሚኛ ቋንቋ ጋር ያላቸው ተዛምዶ ከተነሳንበት የፅሁፉ ዓላማ አንፃር በኋላ የምንመለከታቸው ቢሆንም ሙዳ፣ ሙራና ሙሪ ግን መሰረታዊ የካይዘን ስራ አመራር ፍልስፍና ቴክኒኮች ናቸው። “ካይ” ለውጥ “ዘን” ደግሞ መልካም ወይም የተሻለ የሚለውን ይገልፃል ። ካይዘን የስራ አመራር ፍልስፍና ነው። የተሻለ ለውጥ (change for good) ለማምጣት ጃፓኖች የተጠቀሙበት የለውጥ መሳሪያ ነው። በሀገሩ ቋንቋ Masaaki Imai ማለት የተሻለ ለውጥ እንደ ማለት ነው። ካይዘን በአጭሩ “ዘለቄታዊ መሻሻል” ማለት ሲሆን የሁልጊዜ መሻሻል፣ የሁሉም ሰው መሻሻልና የሁሉም ቦታ መሻሻል የሚሻ የስራ አመራር ፍልስፍና ነው። ካይዘን ጃፓን ከችግር የወጣችበት ፍቱን የለውጥ መሳሪያ እንደሆነም ይነገራል። ጃፓን እንዴት ሰለጠነች? የሚለውን ጥያቄ ሲነሳም “ካይዘን” አብሮ መነሳቱ የተለመደ ነው። “ከሽ ከሽ እንደ ጃፓን ዕቃ” ሲባል የነበረው የምፀት አነጋገር ወደ ጥራት ያሸጋገረውም ካይዘን ነው። ካይዘን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጃፓን ቀምማ ኢንዱስትሪዎቿን ከጥራት ጉድለት ወረርሽኝ የፈወሰችበት መድሃኒት ነው። መድሃኒቱ አሁንም የጃፓን ወዳጆች እየፈወሰ ይገኛል። ሀገራችንም የዚሁ መድሃኒት ተጠቃሚ ለመሆን በጥረት ላይ ትገኛለች። የጃፓን የ40 ዓመት የካይዘን ተሞክሮ በሶስት ምእራፍ ከፋፍሎ ማየት ይቻላል። እ.አ.አ  ከ1955 እስከ 1970 የማሸጋገር፣ ከ1970 እስከ 1990 የማጣጣምና ከ1990 ወዲህ ደግሞ የራስ የማድረግ ስራ ተከናውኗል። ካይዘን በሲንጋፖር በተመሳሳይ ሶስት ምእራፎች ተከፋፍሎ መተግበሩንና ውጤታማ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በአህጉራችንም በግብፅና ቱኒዝያ የማምረቻ ተቋማት የጥራትና የምርታማነት ለውጥ ማምጣቱን በተግባር ተረጋግጧል። ይህ የለውጥ መሳሪያ ወደ አገራችን የገባው በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጥረት ነው። እ.አ.አ 2008 ኦክላሃማ በተካሄደው አራተኛው የጃፓን ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ለአፍሪካ ልማት ላይ የተሳተፉት አቶ መለስ ከወቅቱ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተወያይተው በማስፈቀድ ወደ አገራችን እንዲገባ አደረጉት። በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በሚገኙና በተመረጡ 30 ኢዱስትሪዎች ላይ በሙከራ ደረጃ ለ3 ዓመታት ሲከናወን ቆይቶ የራሱ የሆነ የ15 ዓመታት ፍኖተ ካርታ ከተዘጋጀለት በኋላ ወደ ሙሉትግበራ ተሸጋግሯ። በኢትዮያ የካይዘን ስራ አመራር ኢንስቲትዩት የጥናት፣ ምርምርና ብቃት ማረጋገጫ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኮኮብ ደመቀ እንደገለፁት ፍኖተ ካርታው ሶስት ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ የነበረው ሲሆን በ625 የማምረቻና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ እየተተገበረ ነው። ሁለተኛው እስከ 2012 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የሚከናወን ሲሆን በማስተርስ ዲግሪ ደረጃ በሚገኙ ባለሙያዎች አማካሪነት ይተገበራል። ሶስተኛው ደረጃ ደግሞ እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ይዘልቃል። በዶክትሬት ዲግሪ ባለሙያዎች አማካኝነት እየተመራም  ወደ ፈጠራ ይሸጋገራል። በአገራችን 6ኛ ዓመቱን የያዘው የካይዘን ስራ አመራር ፍልስፍና መተግበር የጀመሩ ተቋማት እስከ አሁን ድረስ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ከብክነት ማዳናቸውን በሰነድ ማስረጃ ጭምር መረጋገጡን አቶ ኮኮብ ይናገራሉ። የካይዘን ባህሪያት አራት ናቸው። ዘላቂነት፣ ተሳትፎአዊ፣ የጥቂት በጥቂትና የበርካታ ለውጦች ድምርና ያለ ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ ፍሰት የሚፈልቅ ማሻሻያ ነው። “ዘላቂነት” አንዱ የካይዘን ባህሪ ሲሆን አቅድ፣ ተግብር አረጋግጥ፣ እርምጃ ውሰድ የሚሉ ዑደቶችን ማለፍ ይጠይቃል። ተሳትፎአዊ ሌላኛው ባህሪው ሲሆን ከላይ ወደታችና ወደ ጎን በባለቤትነት መንፈስ ከልብ መስራትን ይጠይቃል። የከፍተኛ አመራሩ፣ የፈፃሚውና የመካከለኛው አመራር ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ማለት ነው። ሶስተኛው የካይዘን ባህሪ የጥቂት በጥቂትና የበርካታ ለውጦች ድምር መሆኑ ነው። ካይዘን በአንድ ምት ታላቅ ውጤትን ማስመዝገብ አያልምም። ይሁን እንጂ ጥቂት በጥቂት በርካታ ለውጦችን በዘለቄታዊነት በማጋጠም ታላቅ ውጤትን ያስመዘግባል፡፡ ማሳኖሪ ሞሪታኒ የተባለ ፀሀፊ ለዚሁ ማሳያ ይሆን ዘንድ በአንድ የጃፓን የኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ውስጥ የነበረውን ሒደት እንደሚከተለው አስቀምጦታል።  “በ1978 በኩባንያው የአንድ ምርት ወጪ 500 ሺህ ብር ነበር። የካይዘንን ፍልስፍና በመተግበር  በ1980 ወጪው ወደ 50 ሺህ ብር አወረደው። ትግበራውን በማላመድ ደግሞ በ1981 ወጪው 10ሺህ ሆነ። የካይዘን ክንዋኔ ማዝለቅ በመቻሉም  በ1982 ወደ 5 ሺህ ዝቅ አደረገው” ይለናል። አራተኛው የካይዘን ባህሪ ያለ ከፍተኛ መዋዕለ-ንዋይ ፍሰት የሚፈልቅ ማሻሻያ መሆኑ ነው ።ብክነትን ለማስወገድ ገንዘብ አያስፈልግም። ምናልባትም እጅግ አነስተኛ ወጪ ቢፈልግ እንጂ፡፡ ከኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በእኛ አገር አምስቱን “ማ” በፈረንጆች ደግሞ አምስቱን “S” መሰረት ያደረገ የካይዘን ትግበራ አጀማመር ከጥቅሙ አንጻር እጅግ አነስተኛ ገንዘብ ብቻ የሚጠይቅና አዋጪ ነው። አምስቱን “ማ” ማጣራት (sort)፣ ማስቀመጥ(set in order)፣ ማፅዳት (shine)፣ ማላመድ (standardize) እና ማዝለቅ (sustain)ናቸው። ከሁሉም የካይዘን ቴክኒኮች ባነሰ ወጪ ለመተግበር ይጠቅማሉ። ማጣራት (sort) የስራ አካባቢን ያለአግባብ ያጨናነቁ ነገሮችን ወይም ቁሳቁሶችን የምናስወግድበት የ5ቱ “ማ” ዎች የመጀመሪያ ደረጃ ነው። ማስቀመጥ (set in order) ሁለተኛው የአሰራር ስርዓት ሲሆን ለእለቱ ስራ የምንገለገልባቸውን መሳሪያዎች ወይም ግብአቶች እንደየጠቀሜታቸው ለይተን በቅርብ ቦታ የምናስቀምጥበት ነው። ማፅዳት (shine) የ5ቱ “ማ” ዎች ሶስተኛው ደረጃ ሲሆን ከላይ ለስራ ቅልጥፍና በሚረዳን መልኩ በስርዓት ለይተን ያስቀመጥናቸውን የመገልገያ መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች በተገቢው የማፅጃ ቁሳቁስና ዘዴ እየወለወልን በነበሩበት ቦታ የምናስቀምጥበት ሒደት ነው። አራተኛው ደረጃ ማላመድ (standardize) ነው። የፀዳና የተዋበ የስራ አካባቢያችን ተመልሶ እንዳይበከል መገልገያ መሳሪያዎችን የሚለዩበትን፣ የሚቀመጡበትንና የሚፀዱበትን ሒደት በቀጣይነት የምንፈጥርበት ስልት ነው። ለዚህም ማን? ምን? መቼና እንዴት? መተግበር እንዳለበት ወጥ የሆነ መመሪያ ማዘጋጀት ይገባል። አምስተኛው ደረጃ ማዝለቅ (sustain) ሲሆን በየእለቱ ተከታታይነትና ዘላቂነት ያለው የስራ ባህል እንዲፈጠር የምናደርግበት ዘዴ ነው። የማዝለቅ ዋና ዓላማ ሰራተኞች በየእለቱ መከተል ያለባቸውን ሒደት በአእምሮአቸው ውስጥ እንዲያሰርፁ ማድረጊያ ነው። ከላይ የተጠቀሱት ማጣራት፣ ማስቀመጥ፣ ማፅዳትና ማላመድን በዘላቂነት ተግባራዊ እንዲሆኑ የምንጠቀምበት ስልት ነው። አምስቱን “ማ” ዎች በአግባቡ መተግበር የሚቻለው የካይዘን መሰረታዊ ቴክኒኮች የሆኑትን ሙዳ፣ ሙራና ሙሪን በመከላከል ብክነትን በማዳን ነው። ሙዳ (muda) በጃፓንኛ ለምንሰጠው አገልግሎት ወይም ለምናመርተው ምርት ምንም ዓይነት የጥራትም ሆነ የብዛት ለውጥ የማያመጣና እሴት የማይጨምር፣ የስራ ሂደትን የሚያዘገይ፣ በአመራረት ላይ ወጪ የሚጨምር ማንኛውንም አላስፈላጊ ነገር የሚገልፅ ነው። በአማርኛ ደግሞ ብክነት ልንለው እንችላለን። የሙዳ ወይም የብክነት ዓይነቶች ከሚያስፈልገው በላይ ማምረት (“muda” of overproduction)፣ የንብረት ክምችት ብክነት (“muda” of inventory)፣ የመጠበቅ ብክነት (”muda” of waiting )፣ የማጓጓዝ ብክነት (“muda” of transportation )፣ የማምረት ግድፈት ብክነት (“ muda” of defect-making)፣ የእንቅስቃሴ ብክነት (“muda” of motion) እና የአሰራር ብክነት (“muda” in processing) ናቸው። ብክነቶችን ለማስወገድ ደግሞ ብክነቱን በግልፅ እንዲታይ ማድረግ፣ ምን ጊዜም ብክነት እንዳይከሰት በንቃት መከታተል፣ ለሚፈጠር ብክነት ተጠያቂ መሆን፣ ብክነትን መለካትና ብክነትን መቀነስ ወይም ማስወገድ  ግድ ይላል። ሙራ (mura) ሁለተኛው የካይዘን መሰረታዊ ቴክኒክ ሲሆን በአሰራር ላይ ያልተመጣጠነ የስራ ክፍፍል፣ ያልተመጣጠነ የማሽን አቅምና የተለያየ የግብአት አቅርቦት መኖርን የሚያመላክት ነው። ይህ የሚፈጠረው ለሰራተኛ በቂ ስልጠና አለመስጠት፣ በቂ የመለዋወጫ ዕቃዎች አለመኖር፣ የግብአት ጥራት መጓደል፣ አላስፈላጊ እንቅስቃሴና የመገልገያ ዕቃዎችን በአግባቡ አለመጠቀም ሲኖር ነው። ሙሪ (muri) ደግሞ ሰውን ጨምሮ እንስሳትም ሆኑ ማሽኖች ከአቅም በላይ በማሰራትና በማስጨነቅ ጫና የሚያደርስ አሰራር ነው። ማንኛውንም አምራች ሃይል የማምረትና የመንቀሳቀስ አቅሙ ውሱን ነው። ከአቅሙ በላይ እንዲሰራ ከተደረገ ህይወት ያለው አምራች ለበሽታና ለሞት ቁስ አካሉ ደግሞ ለብልሽት ይዳረጋል። ሙሪ የሚፈጠርባቸው በርካታ መንስኤዎች ቢኖሩም የስራ ጫናና የሰራተኛ አለመመጣጠን፣ ለስራው የተመደበው በጀት አነስተኛ መሆን፣ ለሰራተኞች የማይመች አቀማመጥ፣ የስራ ቦታ ደህንነት አለመኖር፣ የአቅርቦት እጥረትና መጓተት እንደሚያስከትል የኢንስቲትዩቱ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህ ዓይነቱ ችግር ምርትን ለመጨመርና ትርፋማ ለመሆን በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ በሰውም ሆነ በማሽን ላይ ጫና መፍጠር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። በሶስቱ የጃፓንኛ ቃላቶች ያየናቸው መሰረታዊ የካይዘን ቴክኒኮች በኛው የኦሮሚኛ ቋንቋ ፍቺ ሰጥተን ሙዳ፣ ሙራና ሙሪ ማስተካከል እንችላለን። ለለውጥ በእምነት ገብተን እንደምንረባረብ በመወሰን የተንዛዙ አሰራሮችን ማሳጠር አሊያም መቁረጥ እንችላለን ብለን መውሰድ አለብን ። ካይዘን እነዚህ ሁሉ በማስቀረት የምርት ጥራትን፣ ምርታማነትን፣ ተወዳዳሪነትንና የሰራተኞች ተነሳሽነትን በማሳደግ ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን የሚናገሩት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ያኢ ናቸው። ፍልስፍናው ካይዘንን ተግባራዊ የሚያደርጉ ኩባኒያዎች ግብአትን ያልተጨመረበት የምርት ሒደትና ብክነትን በመቀነስ የጥራት ደረጃቸውን ማሻሻል እንደሚችሉ በጥናት ተረጋግጧል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በሰራተኞች ላይ ተነሳሽነትን የሚያሳድግ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ ገንቢ ሚና እየተጫወተ በመሆኑ በጥራት፣ በምርታማነትና በተወዳዳሪነት ላይ ጎልቶ የሚታይ ውጤት መታየት መጀመሩን አስረድተዋል። ካይዘን የስራ አመራር ፍልስፍና ተግባራዊ ያደረጉ ኩባኒያዎችም የዋና ዳይሬክተሩን ሓሳብ ይጋራሉ። ሙዳ ፣ ሙራንና ሙሪን በመከላከልና አምስቱን “ ማ” ዎችን ተግባራዊ በማድረግ በርካታ ሀብቶችን ከብክነት ማዳን እንደቻሉ መስክረዋል። ፍልስፍናውን ተግባራዊ ካደረጉ ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት አንዱ ነው። ለፍልስፍናው መተግበሪያ 141 ሺህ 580 ብር በጀት መድቦ 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ከብክነት ማዳን ችሏል። ካይዘን በአነስተኛ ወጪ ብዙ ውጤት የሚገኝበት ፍቱን አማራጭ መሆኑንም በተግባር አረጋግጧል። ኢታብ ሳሙና ፋብሪካም የፍልስፍናው ተጠቃሚ ነው። ፋብሪካው ካይዘንን በመተግበር የሳሙናው ጥራት 98 ነጥብ 02 በመቶ እንዲያደርስ አግዞታል። 242 ሺህ ብር ከብክነት እንዲያድንም አግዞታል። በአንደኛው ደረጃ የካይዘን ስራ አመራር ፍልስፍና ባገኘው ውጤት በመነሳሳትም ለሁለተኛውን ደረጃ ትግበራ እራሱን እያዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል። የካይዘንን ጥቅም በተግባር አረጋግጫለሁ የሚለው ሌላው ኩባኒያ የባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ነው። ማጣራትን፣ ማስቀመጥን፣ ማፅዳትን፣ ማላመድንና ማዝለቅን በመተግበር 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ከብክነት ማዳን ችሏል። የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ትግበራውን ያስገኘው ውጤትና ያጋጠሙትን ተግዳሮት ለመለየት አንድ ዓመት የፈጀ 7 ጥናትና ምርምሮችን አካሔዷል። በጥናትና ምርምር የተረጋገጡ ግኝቶች ደግሞ ከንድፈ ሃሳብ የዘለሉ እንዳይሆኑ በማሰብ ተግባሪ ተቋማትን በማሰባሰብ ከ8 ኩባኒያዎች ልምድ ጋር እንዲዋሃድ አድርጎታል። ንድፈ ሃሳቡን ከተግባር ጋር በማገናዘብ ውጤታማ መሆኑን በመረጋገጡ ደግሞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መግባባት ላይ ተደርሷል። በስፋት ወደ አዳዲስ ተቋማት ጭምር ቢስፋፋ አገርንም ሰራተኛውንም ጭምር ይጠቅማልና በጉጉት ልንጠብቀውና ልንቀበለው ይገባል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም