ለህጻናት መቀንጨር ችግር ተቋማት እኩል ትኩረት አለመስጠታቸው ተገቢው ለውጥ እንዳይመጣ አድርጓል

204

አዲስ አበባ ኅዳር 11 ቀን 2012 በኢትዮጵያ ለህጻናት መቀንጨር ችግር ተቋማት እኩል ትኩረት አለመስጠታቸው የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ ማድረጉን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ የ2011 ዓመት ብሔራዊ የስርአተ- ምግብ መርሃ ግብር አፈጻጸምን ከክልል ጤና ቢሮዎችና  ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በአዲስ አበባ እየገመገመ ነው።

በ2011 እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ያሉ ህጻናት መቀንጨርን ከነበረበት 38 በመቶ ወደ 31 በመቶ ዝቅ ለማድረግ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ማሻሻል የተቻለው አንድ በመቶ ብቻ መሆኑ ተገልጿል።

በመሆኑም የ2019 የስነ ህዝብና ጤና ዳሰሳ ጥናት እንዳመለከተው በኢትዮጵያ የመቀንጨር ችግር 37 በመቶ ላይ ይገኛል።

በቁጥርም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት ለመቀንጨር ችግር የተጋለጡ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ከ5 ሚሊዮን እንደሚሊቅ ያሳያል።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት የስርአተ ምግብ ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም ለኢዜአ እንዳሉት የመቀንጨር ችግር በአንድ ተቋም እንቅስቃሴ ብቻ የሚፈታ አይደለም።

ተቋማቱም የህጻናትን የስርአተ ምግብ ሁኔታ ለማሻሻል የተሰጣቸውን ተግባር በእኩል ባለመፈጸማቸውም የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ አድርጎታል ብለዋል።

በዘርፉ ያለውን ችግር ለመቀነስም የግብርና፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የውሃና ሌሎች ተቋማት የተሰጣቸው ድርሻ ቢኖርም ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ በኩል ግን ልዩነት መኖሩን ጠቁመዋል።

መቀንጨርን ለመቀነስ ታዲያ በአንድ ተቋም ብቻ የሚሰራ ባለመሆኑ በቀጣይ በትብብር መስራት እንደሚጠይቅ ነው የገለጹት ዶክተር መሰረት።

በመቀንጨር ላይ የሚሰሩ ተግባራትን  ከሌሎች እቅዶች እኩል ማቀድ፣ ተጠያቂነትን ማስፈን እንዲሁም የዘርፉ አመራር ቁርጠኝነት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚያስፈልጉ ጉዳዮች ውስጥ መሆናቸውንም  ጠቅሰዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት በከፍተኛ ሁኔታ የመቀንጨር ችግር ካለባቸው አገሮች መካከል መሆኗን አንስተዋል።

ችግሩን ለመፍታትም በ2030 ከ7 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ህጻናትን ከመቀንጨር ለመታደግ የተገባውን የሰቆጣ ቃል ኪዳንን ጨምሮ እንደ አገር እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን ዘርዝረዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ በንጥረ ነገር የበለጸጉ ምግቦችና የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ማሻሻል እንዲሁም የጽንስ ክትትልን ማሻሻል እየተሰሩ ካሉ ተግባራት መካከል ናቸው።

ችግሩ በአጭር ጊዜ የሚፈታ ባለመሆኑም የተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራርና ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ነው በአጽንኦት ያነሱት።

አዲስ አበባ ከተማና ጋምቤላ ክልል መቀንጨር በአንጻራዊነት የተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ትግራይና አማራ ክልል አሁንም ችግሩ በስፋት ከሚስተዋልባቸው መካከል ናቸው ተብሏል።

የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ከ 1 ሚሊየን በላይ ህጻናት የቀጨጩ፣ 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ደግሞ የሰውነት ክብደታቸው ለእድሜያቸው ከተገቢው በታች የሆኑ እንዳሉ ነው።

ለትምህርት መጠነ መድገም ምክንያት ከሚሆኑት ምክንያቶች ውስጥም መቀንጨር 16 በመቶ እንደሚይዝም መረጃው ያሳያል።

ኢትዮጵያ እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በ2030 ማንኛውንም የምግብ እጥረት ለማስቀረትና ከ2 ዓመት በታች ያለውን የመቀንጨር ችግር ዜሮ ማድረስ  የሚል አጀንዳ ይዛ እየሰራች ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም