ቀጥታ፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ሊካሄድ ነው።

አዲስ አበባ 30/2010 በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጣዩ ወር እንደሚካሄድ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር አስታወቀ። ግንቦት 29 ቀን 2010 ዓ.ም የሚካሄደው ይህ ውድድር የአትሌቲክስ ማህበሩ ከተለያዩ አገሮች የስፖርት ሚኒስትሮች፣ የከተማ መስተዳድሮች፣ የውድድር አዘጋጆች፣ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖችና ማህበራት ጋር በትብብር የሚያዘጋጀው ነው። ውድድሩ አንድ ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር(አንድ ማይል) የሚሸፍን ሲሆን የአትሌቲክስ ፍላጎትና ፍቅር ያለው ማንኛውም ተወዳዳሪ መሳተፍ እንደሚችል ተገልጿል። ውድድሩ በ23 አገሮች በሚገኙ 24 ከተሞች የሚካሄድ ሲሆን ከከተሞቹ መካከል የኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ አንዷ ነች። ሲድኒ፣ ቶኪዮ፣ ሳኦፖሎ፣ ቦነስ አይረስ፣ ጆሃንስበርግና ቫንኩቨር ውድድሩ ከሚካሄድባቸው ከተሞች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ። ውድድሩ በሁሉም አገሮች በተመሳሳይ ሰዓት ይጀመራል። የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፕሬዚዳንት ሴባስቲያን ኩ እንደገለጹት ውድድሩ የአትሌቲክስ ፍቅር ያላቸውን በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን የሚያገናኝ ነው። የዓለም ሩጫ ቀንን አስመልክቶ የሚዘጋጀው ይህ ውድድር "ሩጫ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ መሆን አለበት" የሚለው ጥረት አካል እነደሆነም ተገልጿል። ለስፖርቱ ተነሳሽነት ያለው የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚወዳደርበት በመሆኑም ለሌሎችም ሰዎች መነቃቃት ይፈጥራል ተብሏል። "ሩጫ ለሰውነት ጥንካሬ የሚሰጥ፣ ሰዎች ጤናቸውንና የአካል ብቃታቸውን እንዲጠብቁ የሚያደርግ የስፖርቶች ሁሉ እናት ነው" ያሉት የዓለም  ፕሬዚዳንቱ፤ ውድድሩ አዝናኝና አነቃቂ እንደሚሆንም ገልጸዋል። ስፖርቱ ፈታኝና ብርታት የሚጠይቅ ቢሆንም ማህበረሰብን ከማቀራረብ አኳያም ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል። የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሩ "የከተማ መሪ" (city captain) የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን በውድድር ላይ ያለ ወይም ቀድሞ ይወዳደር የነበረ አትሌት ውድድሩን እንደሚመራና አትሌቱ በማህበረሰቡ ውስጥ አትሌቲክስን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት የጎላ ሚና ያለው መሆን እንደሚጠበቅበትም ተጠቅሷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም