የሲዳማ የክልልነት ህዝበ ውሳኔ የድምፅ አሰጣጥ ተጠናቀቀ

103
ህዳር 10/2012 ዛሬ ከማለዳው አስራ ሁለት ሰዓት ጀምሮ ሲካሄድ የዋለው የሲዳማ የክልልነት ህዝበ ውሳኔ የድምፅ አሰጣጥ ተጠናቀቀ፡፡ በሲዳማ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች እና በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በተቋቋሙ 1ሺህ 692 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ድምጽ ሲሰጥ ውሏል። በርካታ ድምጽ ሰጪ በተመዘገበባቸው አካባቢዎች መጉላላት እንዳይኖር 175 ተጨማሪ ጣቢያዎች ተከፍተው ድምፅ ሲስጥ መዋሉን ከድምጽ መስጫያ ጣቢያ አስፈጻሚዎች ለመረዳት ተችሏል። አነስተኛ ድምጽ ሰጪ በተመዘገበባቸው ጣቢያዎች ስነስርዓቱ ከተቀመጠለት አስቀድሞ መጠናቀቁን በስፍራው የሚገኘው ሪፖርተራችን   ገልጿል። ሪፖርተራችን አሁን በሚገኝበት የፊላደልፊያ ቀበሌ ጣቢያ "ሀ" የድምጽ አሰጣጡ ስነስርዓት መጠናቀቁን ተከትሎ ቀሪ ወረቀቶች ተቆጥረው የድምጽ መስጫ ሳጥኑ ሲቆለፍ ተመልክቷል። ከቆይታ በኋላ ቆጠራ እንደሚጀመርና ውጤቱም ነገ ጠዋት ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ታውቋል። ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ውጤቱን በ48 ሰዓት ውስጥ ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም