ህገወጥ ንግድን ለመከላከል ሁሉም የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ተጠየቀ

62
ኢዜአ ህዳር 10/2012፡- በቤንች ሸኮ እና ጌዴኦ ዞኖች እየተባባሰ የመጣው ህገወጥ ንግድ ለመከላከል ሁሉም የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ተጠየቀ። ህገወጥ ንግድን በመከላከልና  በታክስ ህግ  ተገዥነት ችግሮች ዙሪያ በሚዛን አማን እና በዲላ ከተሞች ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄዷል። በሚዛን አማን በተካሄደው ውይይት ከተሳታፊዎች መካከል ከሚዛን አማን ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የመጡት አቶ ጌታቸው ሀብቴ በከተማው ህገወጥ ግብይት እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግረዋል። ችግሩን በአንድ አካል ጥረት ብቻ ማስቆም አይቻልም"  ያሉት አቶ ጌታቸው የባለድርሻ አካላትን የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል። በከተማው የመንገድ ላይ ግብይት እየተበራከተ መምጣቱንና ይህም በህጋዊ ነጋዴዎች ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው። ህገወጦች ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ስርዓት ማሲያዝ እንደሚገባም አመልክተዋል። ኮንትሮባንድና  ሌላም ህገወጥ ግብይት የሚያሳድረው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ለማስቆም የሚጠበቅበት እንዲወጣ የጠየቁት ደግሞ የጉራፋርዳ ወረዳ ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉ ዘካርያስ ናቸው። የቤንች ሸኮ ዞን  ንግድና  ገበያ ልማት  መምሪያ ኃላፊ   አቶ ታምራት ከተማ ያልተገባ  የዋጋ ጭማሪ ምርትን ማከማቸት የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ  ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ መሸጥ እንደሚስተዋል ገልጸዋል። በተደረገው  ቁጥጥርም 1ሺህ 192 በሚሆኑ ነጋዴዎች ምክርና ማስጠንቀቂያ እንደሰጣቸው አመልክተው  250 ሱቆች ደግሞ እንዲዘጉ መደረጉን አስረድተዋል። "ህገወጦችን በማጋለጥ እርምጃ እንዲወሰድ ህብረተሰቡን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት  በጥምረት ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ  በዲላ  በተካሄደው የውይይት መድረክ የጌዴኦ ዞን ገቢዎች ባለሰልጣን ቅርንጫፍ  ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተወልደ ተስፋዬ እንዳሉት የታክስ መሰወር ማጭበርበርና የኮንትሮባንድ ንግድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። በዚህም በዞኑ ባለፉት አራት ዓመታት ወደ መንግሰት ካዝና መግባት የነበረበት  ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አለመሰብሰቡን ጠቅሰዋል።። ይህም በንግዱና በገቢ ሴክተሩ የሚገኙ ባለደርሻ አካላት የህግ ተገዥነት ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑን እንደሚመለክት አስረድተዋል። ከባለድርሻ አካላት መካከል አቶ ሳሙኤል በፍቃዱ  በዞኑ በንግዱና ገቢ ሴክተሮች ወጥ የሆነ ቁጥጥር አለመኖርና የቅጣት መጠኑ ዝቅተኛ መሆን ጋር ተዳምሮ ህገ ወጥ ንግድ እንዲበራከት ምክንያት መሆኑን አንስተዋል የጌዴኦ ዞን ዋና አስተደዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ በዞን የታክስ ማጭበርበርና የኮንትሮባንድ ንግድ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ የባለደርሻ አካላት ሚና የጎላ መሆኑን ተናግረዋል በዞኑ ግብራቸውን በታማኝነት የሚከፍሉ ነጋዴዎች ቢኖሩም አሁን ለሚስተዋለው ህገ ወጥ ንግድና የታክስ ማጭበርበር ስርዓት ለማስያዝ  መረባረብ እንደሚገባ  አሳስበዋል ። በሁለቱም ከተሞች ዛሬ በተካሄደው ውይይት ነጋዴዎች ፣የአስተዳደር አካላት፣ የዘርፉ ስራ ኃላፊዎች፣ ባለሙዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም