ቀጥታ፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ከአውሮፓ ህብረት አባል አገሮች አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ

ህዳር 10/2012 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ከአውሮፓ ህብረት አባል አገሮች አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ስላለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ወቅታዊ ሁኔታ ለአምባሳደሮቹ ገለጻ አድርገዋል ።
 
በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደውን አጠቃላይ ምርጫና የምርጫ ተቋማትን ለማጠናከር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችንና በዛሬው እለት በሲዳማ እየተካሄደ ያለውን ህዝበ ውሳኔ በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
 
ለውጡን ተከትሎ እያጋጠሙ ስላሉ የሰብዓዊ መብት ተግዳሮቶችና የውስጥ መፈናቀል፣ ስለ አገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ስለ አገሪቱ የንግድ ሁኔታ፣ የአፍሪካ ነጻ ገበያ እና በአገር ውስጥ ባሉ አጠቃላይ ሁኔታዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።
 
የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለው አጠቃላይ ትብብር በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን አምባሳደሮቹ በተወካያቸው አምባሳደር ጆሃንቦርግ ሳትም በኩል ገልጸው፤ እየተከናወኑ ያሉ አጠቃላይ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን እንደሚደግፉ ገልጸዋል።
 
በዚሁ አጋጣሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ2019 የኖቤል ሰላም ሽልማትን መቀዳጀታቸው በአገሪቱ የሚከናወኑ አጠቃላይ ለውጦች ማረጋገጫ መሆኑን አምባሳደር ጆሃንቦርግ ሳትም አስታውሰዋል ።
 
አምባሳደሮቹ ኢትዮጵያ በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እየተጫወተች ያለውን ሚና አድንቀዋል።
 
የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ዓመት ምርጫ ለማካሄድ የደረሰበትን ውሳኔም እንደሚደገፉ ገልጸዋል።
 
ለውጡን ተከትሎ በአንዳንድ ቦታዎች የሚታዩ የጸጥታ ችግሮችና የውስጥ መፈናቀሎች፣ ባለሀብቶች ከግብር፣ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ከኢንቨስትመንት ፈቃድ አሰጣጥና ቢሮክራሲዎች ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮችን ለማሻሻል በመንግስት በኩል ያለውን ዝግጁነት በተመለከተ ጠይቀዋል።
 
በተነሱ ጥያቄዎች ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ባለሙያዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
 
በመጨረሻም በአሁኑ ሰዓት በአንዳንድ ቦታዎች የሚታዩ የጸጥታ ችግሮችን ለማስተካከል መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው መሆኑንም አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም