ኤርትራዊያን ስድተኞች በዘመቻ ሰብል እየሰበሰቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኤርትራዊያን ስድተኞች በዘመቻ ሰብል እየሰበሰቡ ነው
ሽረ እንዳስላሴ (ኤዜአ) ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ ም በትግራይ ክልል የሚገኙ ኤርትራዊያን ስደተኞች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የደረሱ ሰብሎችን በዘመቻ በመሰብሰብ ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸው ተገለጸ። ስደተኞቹ በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የደረሱ ሰብሎቹን እየሰበሰቡ ያሉት ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብና የአንበጣ መንጋ ጉዳት ለመከላከል ነው። በእዚህም ኤርትራዊያን ስደተኞች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ለተከታታይ ሦስት ቀናት የአጨዳ ዘመቻ አካሂደዋል። በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን አስተዳደር የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ክብሮም ብስራት ለኢዜአ እንገለጹት ኤርትራዊያን ስደተኞቹ የስልሳ አቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን የደረሰ ሰብል ሰብስበዋል። በዘመቻ ሥራው የተሳተፉ ኤርትራዊያን በዞኑ ማይ ዓይኒ፣ አዲ ሃሩሽ፣ ህፃፅና ሽመልባ መጠልያ ጣቢያዎች የሚገኙ ስድተኞች ናቸው። ኤርትራዊያን ስደተኞች ህዳር 8 ቀን 2012ዓ.ም የጀምሩት የሰብል ስብሰባ ሥራ እስከ ህዳር አጋማሽ ድረስ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አማካሪው ገልጸዋል። በዘመቻው ተሳተፊ የሆነው ኤርትራዊ ስደተኛ ተስፋልደት ክብሮም ስደተኞች በዚሁ በጎ ተግባር መሳተፋቸው የሁለቱን አገራት ህዝቦች ቤተሰባዊ ግንኙነት የሚያጠናክር ከመሆኑ ባሻገር የመንፈስ እርካታ እንደሚሰጥ ተናግሯል። ሌላው የበጎ ተግባሩ ተሳታፊ አቶ ምህርትአብ ክሕሸን በበኩላቸው “የሰላም እጁን ዘርግቶ በፀጋ ለተቀበለን ህዝብ ከጎኑ ቆመን ድጋፍ ስናደርግ ክብር ይሰማኛል” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል። "በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የምርቱ ተጠቃሚ በመሆናችን የደረሱ ሰብሎችን ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብና የአንበጣ መንጋ መታደግ ይገባናል" ያሉው ደግሞ ወጣት መድሃንየ መንግስተአብ ነው። በዞኑ የሚገኙ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባለትን ጨምሮ የተለያዩ የጸጥታ አካላት፣ ተማሪዎችና ማህበረሰቡ ተሳታፊ በሆኑበት የአጨዳ ዘመቻ እስካሁን ድረስ በ119ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ሰብል መሰብሰቡ ቀደም ሲል መገለጹ ይታወሳል።