ዋልያዎቹ የ800 ሺህ ብር ሽልማት ተበረከተላቸው

71
ህዳር 10/2012 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለዋልያዎቹ የስምንት መቶ ሺህ ብር የማበረታቻ ሽልማት አበረከተ። ሽልማቱ የተበረከተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ለ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ትናንት የኮትዲቯር አቻውን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፉ ነው። የፌዴሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ባህሩ ጥላሁን ለኢዜአ እንደገለጹት የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ላስመዘገቡት ውጤት ከ20-30 ሺህ ብር የማበረታች ሽልማት ዛሬ ተበርክቶላቸዋል። በዚሁ መሰረት የቡድኑ አሰልጣኝ 30 ሺህ ብር ተጫዋቾቹም ከ20-25 ሺህ ብር ሽልማት አግኝተዋል። ሽልማቱ ዋሊያዎቹ በቀጣይ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ለማነሳሳት ያለመ ነውም ብለዋል። ዋሊያዎቹ ትናንት በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደረጉት በፈረንጆቹ 2021 በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ለማለፍ ነው። ብሔራዊ ቡድኑ ባለፈው ሣምንት የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታውን ከማዳጋስካር አቻው ጋር አካሂዶ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት መሸነፉ ይታወቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም